በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የደቡብ ሱዳን ጉዳይ እያሰጋ ነው፤ ባን ኪ-ሙን ተናገሩ


ባን ኪ-ሙን - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐ ፊ
ባን ኪ-ሙን - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐ ፊ

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተሞክሮብኛል ያለውን የመንግሥት ግልበጣ ተከትሎ የተነሣው ሁከት ከዋና ከተማይቱ ወሰኖች አልፎ እየተስፋፋ መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ልዑክ - ኡንሚስ
የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ልዑክ - ኡንሚስ


please wait

No media source currently available

0:00 0:05:58 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተሞክሮብኛል ያለውን የመንግሥት ግልበጣ ተከትሎ የተነሣው ሁከት ከዋና ከተማይቱ ወሰኖች አልፎ እየተስፋፋ መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡

ባለፉ ጥቂት ቀናት ውስጥ በተካሄዱ ውጊያዎች ቢያንስ አራት መቶ ሰው መገደሉንና በሺሆች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የባለሥልጣናቱ ግምት ይናገራል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ በእጅጉ እየሳሰባቸው መሆኑን የገለፁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ- ሙን ሁኔታውን ለማረጋጋትና ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አድርገዋል፡፡

ዛሬ፣ የጆንግሌ ክፍለሃገር ዋና ከተማ በሆነችው ቦር ከተማ አቅራቢያ በሚገኙ ሁለት የጦር ሠፈሮች ላይ የመንግሥቱ ወታደሮች መጋጨታቸውን የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ገልፀዋል፡፡

ዛሬ መግለጫ የሰጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን ሁኔታው በጣም እያሳሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ሁከቱ እንዲያበቃ ለማድረግ፣ ሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት መጠበቃቸውንም ለማረጋገጥ የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ትናንት ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ደውዬ ጠይቄአቸዋለሁ፡፡ ከፖለቲካ ተቃዋሚዎች ጋርም ወደ ንግግር እንዲገቡ አሳስቤአቸው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ወደ እንዲህ ዓይነቱ ውይይት ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ዛሬ መስማቴ አስደስቶኛል፡፡” ብለዋል ሚስተር ባን፡፡
ባን ኪ-ሙን - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐ ፊ
ባን ኪ-ሙን - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐ ፊ

የፖለቲካ ችግር እንደመሆኑ ሊሰጠው የሚገባውም የፖለቲካ መፍትሔ መሆኑን የጠቆሙት ሚስተር ባን የፀቡን መዛመት አዝማሚያ እንደሚፈሩም ሲናገሩ “አንዳንድ ምልክቶችን እንዳየነው ሁከቱ ወደ ሌሎች ግዛቶችም የመዛመት አደጋ ያለው ነው” ብለዋል፡፡

በሁከቱ ምክንያት በርካታ ሲቪሎች መፈናቀላቸውን፣ ሁኔታው ውጥረት በጣም የበዛበት እንደሆነና ዛሬ ማለዳ ላይ ከባድ ውጊያ መጀመሩን ተያይዞም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች በቦር ደቡብ ምሥራቅ ጫፍ ላይ ወደሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት ግቢ መጉረፍ መጀመራቸውን የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ልዑክ የኡንሚስ ቃል አቀባዩ ጆ ኮንትሬራስ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ተፈፅሟል የተባለውን ግድያና ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ሁኔታ ድርጅታቸው እያጣራ መሆኑን የተናገሩት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን ድርጅታቸው ሥራውን እያከናወነ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
ተፈናቃዮችና ሁከት የሸሹ በጁባ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው የኡንሚስ ግቢ - ማክሰኞ፣ ታኅሣስ 8/2006 ዓ.ም
ተፈናቃዮችና ሁከት የሸሹ በጁባ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ አቅራቢያ በሚገኘው የኡንሚስ ግቢ - ማክሰኞ፣ ታኅሣስ 8/2006 ዓ.ም

“ልዑካችን ጁባ በሚገኙት ሁለቱ ግቢዎቹ ውስጥ ሲቪሎቹን መርዳቱን ይቀጥላል፡፡ በእነዚህ ግቢዎች ውስጥ ወደ ሃያ ሺህ የሚጠጉና በጆንግሌይ ደግሞ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አሉ” ብለዋል ዋና ፀሐፊው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኡንሚስ ቃልአቀባዩ ኮንትሬራስ የጁባና አካባቢዋን ለሁለት ቀናት የዘለቀ ሁከት ተከትሎ በስተምሥራቅ ከኢትዮጵያ ድንበር ጋር ኩታ ገጠም በሆነው ምሥራቅ ኢኳቶሪያ ክፍለሃገር ዋና ከተማ ቶሪት ውስጥም ግጭቶች እንደነበሩ የሚናገሩ ሪፖርቶች የደረሷቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሳልቫ ኪር - የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት
ሳልቫ ኪር - የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት
“የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ሞክረውብኛል” ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከሚጠሩት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እስከአሁን ቢያንስ አሥር የመንግሥቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል፡፡

ምንም እንኳ ሪክ ማቻር የሳልቫ ኪርን አስተዳደር በመተቸት ድምፃቸው ጎላ ብሎ የሚሰማ ሰው ይሁኑ እንጂ እስከአሁን ከዕይታ እንደተሰወሩ መሆናቸው ነው የሚታወቀው፡፡

ደቡብ ሱዳን የሚገኘው ገለልተኛ የምርምር ተቋም “ሱድ ኢንስቲትዩት” ባልደረባው ጆክ ማዱት ጆክ ምንም እንኳ ማቻር እና ባልንጀሮቻቸው ፕሬዚዳንቱን በአደባባይ ሲቃወሙ ይቆዩ እንጂ መንግሥትን ለመገልበጥ ሞከሩ የሚባለው ነገር ግን በጣም እንደሚያጠራጥራቸው ይናገራሉ፡፡

“በተዘበራረቀና በጣም ተዝረከረከ ሁኔታ የተካሄደው እንቅስቃሴ በአግባቡ የታቀደ ግልበጣ ለማካሄድ የሚያስችል አይደለም፡፡ በዚያ ላይ የሚወነጀሉት ሰዎች መፈንቅለ መንግሥት የማካሄድ ፍላጎት ጨርሶ እንደሌላቸውና እነርሱ የሚፈልጉት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚጨበጥ የፖለቲካ ሽግግር መሆኑን ተናግረዋል” ብለዋል ጆክ፡፡

ምንም እንኳ ዋና ከተማይቱ ጁባ ውስጥ ውጥረቱ አሁንም እንዳየለ ቢሆንም አንፃራዊ መረጋጋት መኖሩ ታውቋል፡፡ ባለፉት ሦስት ቀናት በተካሄደው ውጊያ ወደ አምስት መቶ የሚሆን ሰው መገደሉንና ከሃያ ሺህ በላይ መፈናቀሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል፡፡
ጆንግሌይ ክፍለሃገር - የሰላማዊው ሰው መፈናቀል
ጆንግሌይ ክፍለሃገር - የሰላማዊው ሰው መፈናቀል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐ ፊ ባን ኪ-ሙን በዛሬው መግለጫቸው በአካባቢያዊ የመሪነት ተደማጭነታቸው የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ ሁኔታውን መልክ ለማስያዝ የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ዛሬ ደውለው የጠየቋቸው መሆኑንና ልዩ ልዑካቸው ሂልደ ጆንሰንም በቅርብ መከታተላቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ በዚሁ በዛሬው መግለጫቸው በተደጋጋሚ የጠየቁት ሚስተር ባን የታሠሩ ሰዎች ጉዳይና የወታደሮችም እንቅስቃሴ የቅርብ ክትትል እንዲደረግበት አሳስበዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ በዚሁ መልዕክታቸው “የተያዙ ሰዎች ሁሉ ሰብዓዊ መብቶችን መጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ኃላፊነት የተሰጣቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ጉዳዮች ተከታታዮች እሥረኞቹን በቅርብ እንዲጎበኝዋቸው ሙሉ ነፃነት እንዲኖራቸው መፈቀድ አለበት፡፡ የፀጥታ ኃይሎችም መንቀሳቀስ ያለባቸው ከዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር ሙሉ በሙሉ በሚጣጣም መንገድ ነው” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ሃገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት እየተጣደፉ ባሉ መንገደኞች ተጨናንቆ በሚገኘው የጁባ አየር ጣቢያ አካባቢም ዛሬ ውጊያ መቀስቀሱን ዘገባዎቹ አመልክተዋል፡፡

በዩጋንዳ ወሰን ላይ ደግሞ የኒሙሌን ኬላ ለመሻገር በመቶዎች የሚቀጠሩ ተሽከርካሪዎች የድንበር መተላለፊያው እስኪከፈትላቸው ተሰልፈው ውለዋል፡፡

ባለሥልጣናቱ ኬላውን መቼ እንደሚከፍቱ አልተናገሩም፡፡ መንገደኞቹ ግን ገንዘብም ቀለብና ሌላ ስንቅም እየጨረሱ መሆናቸውን በስጋት እየገለፁ ነው፡፡
XS
SM
MD
LG