በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ የጎርፍ አደጋ 21 ሰዎች ሞቱ


በጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ የጎርፍ አደጋ 21 ሰዎች ሞቱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:51 0:00

በደቡብ ክልል ጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ በተከሠተ የጎርፍ አደጋ፣ 21 ሰዎች ለኅልፈት ሲዳረጉ፣ ከ5ሺሕ800 በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የዞኑ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

በተከሠተው የጎርፍ አደጋ፣ 10 ሰዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶር. ጌትነት በጋሻው ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ኀሙስ፣ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በጎፋ ዞን ኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ፣ ዛባ በምትባል ቀበሌ በደረሰ የጎርፍ አደጋ፥ ለሞት፣ ለአካል ጉዳት እና ለተፈናቃይነት የተዳረጉ ሰዎች መኖራቸውን፣ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዶር. ጌትነት በጋሻው ተናግረዋል። በአደጋው ሕይወታቸው ያለፉ ነዋሪዎች ቁጥር፣ 21 መድረሱንም አስታውቀዋል።

የዞኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሓላፊ አቶ ካሳሁን ዓባይነህ፣ ከ5ሺሕ800 በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ይገልጻሉ።

በጎርፍ አደጋው መሞታቸው ከታወቁት 21 ሰዎች ውጭ የአስከሬን ፍለጋው በአሁኑ ወቅት መጠናቀቁን የተናገሩት አቶ ካሳሁን፣ አንድ እናት ግን የደረሱበት አለመታወቁን ገልጸዋል።

ዘመዶቻቸው በጎርፍ አደጋው እንደሞቱባቸው የተናገሩት የዛባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሮዚያ መሐመድ፣ የተረፉበትን አጋጣሚና አሁን ያሉበትን ኹኔታ አስረድተዋል፡፡

ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያፈሩት ንብረት እንደወደመባቸውና ቤታቸው በጎርፍ እንደተወሰደባቸው የተናገሩት አቶ ሙሴ ቃቆ፣ “ያልጠበቅኹት ዱብዳ ደርሶብኝ ከቤተሰቤ ጋራ ችግር ላይ ወድቄአለኹ፤” ሲሉ፣ ለጊዜው ከተጠለሉበት ቤተ ክርስቲያን ኾነው በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“የደረሰው አደጋ ከፍተኛ፣ ጉዳቱም አሳዛኝ ነው፤” የሚሉት የዞኑ አስተዳዳሪ ዶር. ጌትነት፣ የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት ትምህርት ቤት እና ቤተ ክርስቲያን፣ ሰብአዊ ድጋፍ ማድረግ መጀመሩን አመልክተዋል።

በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙና በጥሩ ሁኔታ ናቸው ሲሉ ዶክተር ጌትነት በጋሻው ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG