በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሠራተኞችን ደመወዝ ለማዳበሪያ ዕዳ ግዢ በዋስትና ያስያዙ የወረዳ አስተዳደር ሓላፊዎች ተከሠሡ


የሠራተኞችን ደመወዝ ለማዳበሪያ ዕዳ ግዢ በዋስትና ያስያዙ የወረዳ አስተዳደር ሓላፊዎች ተከሠሡ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:06 0:00

በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ፣ ከመምህራን በስተቀር አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ፣ ለተከታታይ ሦስት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸውና ከዚኽም የተነሣ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ። የተቋረጠው ደመወዛቸው እንዲከፈላቸው፣ በሰላማዊ ሰልፍ ከጠየቁ ሠራተኞች መካከል፣ ከ200 በላይ የሚኾኑቱ መታሰራቸውን፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ ፋይናንስ ጽሕፈት ቤት፣ ከግለሰቦች እና ከባለሀብቶች ተበድሮ ለተወሰኑት መክፈሉንና ከ200 በላይ የሚኾኑ የ16 መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ግን እንዳልተከፈላቸው አስታውቀዋል።

የሃዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ፣ በመጠኑ ቢለያይም ችግሩ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች መኖሩን አረጋግጠዋል።

የክልሉ መንግሥት፣ የአፈር ማዳበርያ በብድር ሲገዛ፣ የመንግሥት ሠራተኞችን ደመወዝ አካውንት በዋስትና በማስያዙ የተፈጠረ ችግር መኾኑን ጠቅሰው፣ የአሠራር ጥሰት ተፈጽሟል፤ ጥሰቱን የፈጸሙ የዞንና የወረዳ አመራሮች እና ባለሞያዎች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጋቸውን፣ የዞኑ አስተዳዳሪ አብርተዋል፡፡

የዞኑ የመንግሥት ሠራተኞች በማይመለከታቸው ጉዳይ ለምን እንዲቸገሩ ይደረጋል በሚል የተጠየቀው፣ የክልል ፋይናንስ ቢሮ፣ የዞንና የወረዳ ደመወዝ መክፈል እንደማይመለከተው ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የሁሉንም ሠራተኞች ዓመታዊ ደመወዝ ጨምሮ የዞኖቹ ሁሉም ወረዳዎች አጠቃላይ በጀት፣ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ መላኩን ያወሳው የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ፣ ለአርሶ አደሮች የተሠራጨውን የአፈር ማዳበርያ ገንዘብ ሰብስቦ መመለስ፣ የዞኖቹ እና የወረዳዎቹ ሓላፊነት እንደኾነ አመልክቷል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን፣ በሃዲያ ዞን የምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኛ የኾኑ አስተያየት ሰጪ፣ ለተከታታይ ሦስት ወራት ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል።

በወረዳው የግብርና ጽሕፈት ቤት ሠራተኛ መኾናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ምኞት አለነ፣ ከሁለት ወራት መዘግየት በኋላ ደመወዝ እንደተከፈላቸው ጠቅሰው፣ ያልተከፈላቸው ሠራተኞች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ለወራት ያለደመወዝ የቆዩ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ከመቸገራቸው የተነሣ፣ የቤት ዕቃዎቻቸውን ለመሸጥ እየተገደዱ መኾናቸውን ገልጸዋል።

በወረዳው የተለያዩ ዘርፎች ሠራተኞች፣ አስከፊ ሲሉ ወደገለጹት ኢኮኖሚያው እና ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ መግባታቸውን የሚያመለክቱት ሌላው ቅሬታ አቅራቢ አቶ ብሩክ ነዳሞ፣ ደመወዛቸው በወቅቱ እንደማይከፈላቸው ተናግረዋል።

የሃዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ፣ ችግሩ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች መኖሩን አረጋግጠው፣ የምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳን ተነጋግረን፣ ሰሞኑን ለሁሉም ሠራተኞች ከፍለናቸዋል፤ ሲሉ ተናግረዋል።

የምን ያህል ሠራተኞች ደመወዝ እንደተከፈለ የተጠየቁት የምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ የፋይናንስ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ አብርሃም ለራሞ፣ ከግለሰብ እና ከባለሀብቶች ተበድረው ለተወሰኑ ሠራተኞች ክፍያ መፈጸማቸውንና አሁንም ያልተከፈላቸው ስለ መኖራቸው ገልጸዋል።

ከተቋረጠባቸው የሦስት ወር ደመወዝ ውስጥ፣ የአንድ ወሩ ብቻ ለተወሰኑ ሠራተኞች ሰሞኑን እንደተከፈላቸው የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ አብዛኞቹ እንዳልተከፈላቸውና ከፍተኛ ችግር ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም ሠራተኞቹ፣ ደረሰብን ያሉትን በደል፣ ሕዝብ እና የመንግሥት አካላት እንዲያውቁት ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣታቸው ለእስር መዳረጋቸውንገልጸዋል።

የሃዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሩ አቶ አብርሃም ቁጥራቸውን ባይጠቅሱም፣ የታሰሩ ሠራተኞች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፣ የታሰሩት ግን በወንጀል ድርጊት በመሳተፋቸው ነው፤ ብለዋል።

አቶ ብሩክ ግን፣ ደመወዛችን በወቅቱ ይከፈለን ከማለት በቀር የፈጸምነው የወንጀል ድርጊት የለም፤ ሲሉ ይከራከራሉ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም፣ የችግሩ መነሻ፥ ከውዝፍ የአፈር ማዳበርያ ዕዳ ጋራ የተገናኘ መኾኑንና የኦዲት ግኝት ስለመኖሩም አስረድተዋል፡፡ ይህም፣ ከአምስት ዓመታት በፊት አንሥቶ ሲንከባለል የመጣ ችግር የተፈጠረው፣ በወቅቱ የወረዳው ሥራ አስፈጻሚዎች እና አመራሮች ስሕተት እንደኾነና በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉን አቶ አብርሃም ገልጸዋል፡፡

አቶ አብርሃም፣ አርሶ አደሩ በተጠቀመው ማዳበሪያ እና የወረዳውአመራሮች በፈጸሙት የአሠራር ስሕተት፣ ስለምን የመንግሥት ሠራተኞች ይበደላሉ፤ በሚል ለተጠየቁት፣ የክልሉን የፋይናንስ ቢሮ ተወቃሽ ያደርጋሉ።

የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዲሬክተር አቶ አማን ሬሽድ፣ ቢሮው፥ የዞንና የወረዳ ደመወዝ ክፍያ አይመለከተውም፤ ብለዋል።

በዓመቱ መጀመሪያ፣ የሁሉም ሠራተኞች ዓመታዊ ደመወዝ ጨምሮ አጠቃላይ በጀት ተልኳል፤ ለአርሶ አደሮች የተሠራጨውን አፈር ማዳበርያ ገንዘብ ሰብስቦ መመለስ፣ የዞኖች እና የወረዳዎች ሓላፊነት ነው፤ ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል(ሲዳማን ጨምሮ) ከመበታተኑ በፊት፣ ከ2005 እስከ 2010 ዓ.ም. የተወዘፈው 5ነጥብ6 ቢሊዮን ብር የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ እንደነበረበት ተገልጿል።

በዕዳ ውዝፉ የተነሣ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ መክፈል የተሳነው የምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳም፣ ተከፍሏል የተባለውን ጨምሮ ከአጠቃላይ ውዝፉ 61 ሚሊዮን ብር ዕዳ እንዳለበት ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG