በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሃዲያ ዞን ደመወዝ በወቅቱ እንዲከፈላቸው የጠየቁ የመንግሥት ሠራተኞች ታሰሩ


በሃዲያ ዞን ደመወዝ በወቅቱ እንዲከፈላቸው የጠየቁ የመንግሥት ሠራተኞች ታሰሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:50 0:00

በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ፣ ደመወዛቸው በወቅቱ እንዲከፈላቸው ጥያቄ ያቀረቡ የመንግሥት ሠራተኞችን ጨምሮ 40 ሰዎች መታሰራቸውን፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ሠራተኞች ገለጹ።

ከመምህራን በስተቀር አብዛኞቹ የመንግሥት ሠራተኞች፣ አሁንም ለተከታታይ ሦስት ወራት ደመወዝ ስላልተከፈላቸው፣ ለከፍተኛ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር መጋለጣቸውን አመልክተዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ፣ የምሥራቅ ባደዋቾ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ቀደም ሲል፣ ወርኀዊ ደመወዛቸው ወቅቱን ጠብቆ እንዲከፈላቸው ለተከታታይ ወራት ያቀረቡት ማመልከቻ ተቀባይነት ባለማግኘቱ፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ አቤቱታቸውን ለብዙኃን መገናኛ በማሰማታቸው፣ በወረዳው አስተዳደር፣ ተጨማሪ የመብቶች ጥሰቶች እንደተፈጸመባቸው አስታውቀዋል።

በዚኽም ሳቢያ፣ 40 ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ከእነርሱም መካከል 18ቱን ግለሰቦች እንደሚያውቋቸው የጠቀሱት ሠራተኛው፣ ግለሰቦቹ፥ በእስር ከአንድ ወር በላይ ቢያስቆጥሩም፣ እስከ አሁን ክሥ እንዳልተመሠረተባቸው ጠቁመዋል።

በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ ነን፤ ያሉት ሌላው ሠራተኛ አቶ ብርሃኑ አበበ፣ የሚደርስባቸውን በደል እና ጫና እንኳን እንዳይናገሩ መከልከላቸውን ገልጸዋል። “የፌዴራል መንግሥት እና ገለልተኛ አካል ችግሩን ይፍታልን፤” ሲሉ አቶ ብርሃኑ ተማፅነዋል።

ከወረዳው የመንግሥት ሠራተኞች አንዱ አቶ ብሩክ ናዳሞ እንደገለጹት፣ ሠራተኞች ደመወዝ ስለማይከፈላቸው፥ የቤት ኪራይ እና ወርኀዊ የአስበዛ ወጪ መሸፈን አለመቻላቸውንና ልጆቻቸውም መጎሳቆላቸውን፣ በአጠቃላይ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያው እና ማኅበራዊ ችግር መጋለጣቸውን አስረድተዋል።

ከመንግሥት ወገን ምላሽ ለማግኘት፣ ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ፣ ለዞኑ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ሻለቃ ተሾመ ባትሶ፣ እንዲሁም ለዞኑ የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ሓላፊ አቶ ሳሙኤል ሹጉጤ ስልክ ብንደውልም፣ ስብሰባ ላይ እንደኾኑ በመግለጽ እና ቀጠሮ ከሰጡ በኋላ ስልካቸውን በማጥፋት፣ ለማግኘት በመቸገራችን አስተያየታቸውን ለማካተት አልቻልንም።

ይኹን እንጂ፣ ከአንድ ወር በፊት፣ በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጡት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ፣ የሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ ችግር፣ ከዓመታት በፊት ለአርሶ አደሮች ከተሠራጨው የአፈር ማዳበርያ ግዥ ዕዳ ከፈላ ጋራ የተገናኘ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከዚኹ ጋራ በተገናኘ ሰዎች መታሰራቸውን አምነው፣ እስሩ፣ “በወንጀል ድርጊት በመሳተፋቸው ነው፤” ማለታቸው ይታወሳል።

የባደዋቾ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች ግን፣ ወርኀዊ ደመወዛቸው በወቅቱ እንዲከፈላቸው ከመጠየቅ በቀር፣ የተሳተፉበት የወንጀል ዐይነት አለመኖሩን በመግለጽ፣ አሁንም መብታቸው ተጠብቆ ለጥያቄያቸው ምላሽ እንዲሰጣቸው አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG