በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ደቡብ ሱዳን የጦር ወጀል ችሎት በአስቸኳይ እንድታቋቁም ተጠየቀ


አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሎጎ
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሎጎ

የአፍሪካ ኅብረት ለረጅም ግዜ ሲጠበቅ የነበረውንና በደቡብ ሱዳን ሊቋቋም የታሰበውን የጦር ወጀል ፍ/ቤት ለመምሥረት ተግቶ እንዲሰራ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ረቡዕ ጥሪ አድርጓል።

ችሎቱ በአገሪቱ ለአምስት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት ተፈጸመዋል የተባሉ አሰቃቂ ድርጊቶችን ለመመልከት የታሰበ ነው።

በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሊመሠረት ስለታሰበው የጦር ችሎት መጀመሪያ ሥምምነት ተደርሶ የነበረው በእአአ 2015 በተፈረመው የሠላም ሥምምነት ወቅት ሲሆን፣ በኋላም እንደገና በ2018 በነበረው የሠላም ውይይት ላይም ሥምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ሆኖም ግን እስከ አሁን ተግባራዊ ሳይደረግ ቀርቷል።

የመንግሥትና የአማጺያን ወታደሮች በቡድን በመድፈር፣ የዘር ጭፍጨፋ፣ እንዲሁም ሕጻናትን ለወታደርነት በመመልመልና ሌሎች ዘግናኝ ድርጊቶችን በመፈጸም ይወነጀላሉ። በዓለም “ወጣቷ” ተብላ በምትገለጸው አገር በተካሄደው ጦርነት 400ሺህ ሰዎች አልቀዋል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የአምንስቲን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በሲቪል ማኅበረሰብና በእምነት ተቋማት የተመሠረትውና ‘የደቡብ ሱዳን የሽግግር ፍትህ ቡድን’ የተሰኘው ተቋም “የአፍሪካ ኅብረት ለአንድ ፍ/ቤት ሥልጣን ሰጥቶ በአህጉሪቱ የተፈጸመውን አስከፊ ወንጀል እንዲመረምር ማድረግ አለበት ሲሉ አሳስቧል።

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተለይታ አገር በሆነች ሁለት ዓመት ውስጥ ፕሬዚዳንቷ ሳልቫ ኪር ምክትላቸው የሆኑት ሪክ ማቻር የመንግሥት ግልበጣ አሲረውብኛል ብለው ከከሰሱ በኋላ አገሪቱ ወደ ከባድ ጦርነት ውስጥ ገብታለች።

ጦርነቱ በተለይ የብሔር ቅርጽ በመያዙ፣ በማቻር ኑወር ማኅበረሰብና በሳልቫ ኪር ዲንካ ጎሳ መካከል ጨካኝ የሆነ የዘር ግጭት ተከስቷል።

የተመድ መርማሪዎች የዘር ማጽዳት ሳይካሄድ አይቀርም ብለው በማስጠንቀቅ፣ አስገድዶ መድፈርና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ውለዋል፣ ሲቪሎችም በጅምላ ተገድለዋል ሲሉ አክለዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት የሠላም ሥምምነት እንደገና ሲፈረም፣ ሳልቫ ኪር ሥልጣንን የሚያጋራ መንግስት ለመመሥረትና በአፍሪካ ኅብረት በሚቋቋም ፍ/ቤት አስከፊ የተባሉትን ወንጀሎች ለመዳኝት ተስማምተው ነበር።

መንግሥታቸው ግን እንዲህ ዓይነቱን ሂደት በማደናቀፍና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ የማቅረቡን ሥራ በማስተጓጎል በመከሰስ ላይ ይገኛል።

XS
SM
MD
LG