በፑንትላንድ የፀጥታ ኅይሎች ከአይሲስ ታጣቂዎች ጋራ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በተባለ ባደረጉት ውጊያ ቢያንስ ሁለት የቡድኑ ዓባላት መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ቡድኑ በካማካዚ ድሮኖች ሊፈጽም ያቀደውን ጥቃት ማክሸፋቸውንም የሶማሊያ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
አይሲስ በሶማሊያ በመቶ የሚቆጠሩና ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተወጣጡ ተዋጊዎች ሲኖሩት፣ ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያውያን፣ ሱዳናውያን እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ዓባላት እንደሚገኙበት የሶማሊያ ባለሥልጣናት ጨምረው አስታውቀዋል።
የፀጥታ ኅይሎች ከአይሲስ ተዋጊዎች ጋራ ሲዋጉ እንዲሁም ሁለት ተገድለዋል የተባሉ ተዋጊዎችን ያሳያሉ ያሏቸውን ፎቶዎች የፑንትላን ባለሥልጣናት አጋርተዋል።
ፑንትላንድ በመቶ የሚቆጠሩ ኅይሎቿን አይሲስን ለመፋለም ባለፈው ወር አሰማርታለች፡፡
ዘመቻው የመጀምሪያ ደረጃ እንደሆነ የገለጹት ባለሥልጣናቱ በዳዳር ከሚገኘው የአይሲስ መሠረት ገና እንዳልደረሱም አስታውቀዋል። የሶማሊያ መንግሥት የፑንትላንድን ጥቃት አድንቋል።
በሶማሊያ የሚገኘው አይሲስ የተመሰረተውና የሚመራው በእ.አ.አ 2015 ከአልሻባብ አፈንግጦ በወጣው ሼክ አብዱልቃድር ሙሚን ሲሆን፣ አሜሪካ ባለፈው ግንቦት በመሪው ላይ ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ብትግለጽም የአካባቢው ባለሥልጣናት ግን መሪው ከጥቃቱ መምለጡን ይናገራሉ።
መድረክ / ፎረም