በኢትዮጵያ በማኅበራዊ የትስስር ብዙኃን መገናኛ ላይ እግድ ከተጣለ፣ አራተኛ ወሩን ይዟል። በአገሪቱ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያላቸው የፌስቡክ፣ የቲክቶክ፣ የቴሌግራም እና የዩቱብ የማኅበራዊ መገናኛ ትስስር መድረኮች እና ገጸ ድር፣ ከ120 ቀናት በላይ እንደታገዱ ይገኛሉ።
እግዱ፥ እንደ ሉና ሰሎሞን፣ በማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛ ላይ ተጽእኖ በመፍጠር፣ ለልዩ ልዩ ምርቶች እና ተቋማት ማስታወቂያ የሚሠሩ ወጣቶችን ንግድ እየተገዳደረ ይገኛል፡፡ ሉና፣ በቪ.ፒ.ኤን እየተጠቀመች ሥራዋን ለማከናወን ብትችልም፣ የተደራሽነት አድማሷ ላይ ግን ውስንነት ፈጥሮብኛል፤ ትላለች፡፡ “ቪ.ፒኤ.ን ስንጠቀም፣ ዘወትር እየተጠቀምንበት ያለነውን ሀገር እየቀያየረ ያመላክታል፡፡
ስለዚኽ፣ ተመልካቹም በዚያው መሠረት ይወሰናል፡፡ የምንፈልገው ሰው ዘንድ ሁሉ ስለማይደርስ፥ ተሳትፎው፣ የተመልካቾች ቁጥር እና እና የገጹ ተደራሽነት ይቀንስብናል፤” ያለችው ሉና አያይዛም፣ “የምናገኛቸው ገቢዎች፣ በተለይ በዶላር ሲኾኑ፣ ፔይ ፓልም ይኹን ሌሎች የመገበያያ መተገበሪያዎችን በመጠቀም፣ ብር ለማውጣት አንችልም፤” ስትል አክሎቹን አስረድታለች፡፡
እ.ኤ.አ በ2010፣ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት፣ በፌስቡክ እና በወቅቱ በነበሩት የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ አማካይነት ከተቀጣጠለው “የአረብ ጸደይ” ተብሎ ከሚጠራው አብዮት በኋላ፣ ዐያሌ የዓለም መንግሥታት፣ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያም፣ በተለያዩ ጊዜያት፥ የፖለቲካ፣ የብሔር እና የሃይማኖት ግጭቶች፣ እንዲሁም አለመግባባቶች ሲኖሩ፣ የበይነ መረብ አገልግሎት መቋረጡ ዐዲስ አይደለም። ባለፈው የካቲት ወር፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ጋራ ተያይዞ፣ “የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ታይቷል፤” በሚል እና ኀዘናቸውን ለመግለጽ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች እና ምእመናን ጥቁር የመልበስ፣ እንዲሁም የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ ገጾቻቸውን የማጥቆር ሰላማዊ ተቃውሞ አሳዩ።
ይህንኑ ተከትሎም፣ የካቲት 2 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ ቴሌግራም እና ፌስቡክ፣ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ የዩቱብ የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ተዘግተዋል። ይህም እግድ፣ በማደግ ላይ በነበረው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ላይ አሉታዊ ጫና ማስከተሉን፣ የዲጂታል እና ትራንስፎርሜሽን ኢትዮጵያ ማኅበር ምክትል ዲሬክተር አቶ ባሕሩ ዘይኑ፣ በአገሪቱ፣ ከ30 ሚሊዮን በላይ የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ እነኚኽ ተገልጋዮች፣ የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎችን ለመጠቀም፣ የቪ.ፒ.ኤን አገልግሎትን ለማብራት መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡
ከዚኽም ባሻገር ኹኔታው፣ ሌሎች ተጓዳኝ ተጽእኖዎችን እንዳስከተለና በተለይም በአገሪቱ እየተነቃቃ የመጣው የኤሌክትሮኒክስ ግብይት፣ ቪፒኤን ከመጣ በኋላ፣ አገልግሎቱን ለማግኘት ውድ በመኾኑ፣ “የተጠቃሚዎች ቁጥር እየቀነሰ ሔዷል፤” ይላሉ፡፡
እንደ ሀገር ከተመለከትነው፣ የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ፣ በጣም ቀላሉ የመገበያያ መንገድ ነው፤” የሚሉት ባለሞያው፣ አያይዘውም፣ “መንግሥት፣ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮቹን በሚዘጋበት ሰዓት፣ እነዚኽ ሁሉ ጥቅሞች ይቀራሉ፡፡ በገንዘብ መተመኑ አስቸጋሪ ነው የሚኾነው፡፡ ያ ጠለቅ ያለ ጥናት ይሻል፤”
እ.አ.አ. በ2022፣ አገሪቱ፣ በትግራይ ክልል ላይ ባደረገችው የኢንተርኔት አገልግሎት ማቋረጥ፣ 146 ሚሊዮን ዶላር ማጣቷን፣ “ቶፕ ቪ.ፒ.ኤን” የተሰኘ ተቋም ያወጣው ሪፖርት አመልክቷል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ፣ በአሁን ሰዓት፣ ከማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ መቋረጥ እያጣችው ያለው የገንዘብ መጠን፣ በተጣራ መልኩ ባይጠናም፣ ያሳደረው ተጽእኖ ግን፣ የማይናቅ እንደኾነ፣ በእንግሊዝ ሀገር ኤደንብራ ከተማ፣ ሄሪየት ዋት ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ እና የፋይናንስ እና የምጣኔ ሀብት ባለሞያ አብዱልመናን መሐመድ ያስረዳሉ፡፡
“እንደ ሀገር ከተመለከትነው፣ የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ፣ በጣም ቀላሉ የመገበያያ መንገድ ነው፤” የሚሉት ባለሞያው፣ አያይዘውም፣ “መንግሥት፣ የማኅበራዊ ትስስር መድረኮቹን በሚዘጋበት ሰዓት፣ እነዚኽ ሁሉ ጥቅሞች ይቀራሉ፡፡ በገንዘብ መተመኑ አስቸጋሪ ነው የሚኾነው፡፡ ያ ጠለቅ ያለ ጥናት ይሻል፤” ይላሉ፡፡
አብዱልመናን፣ እገዳውን የጣለው የመንግሥት አካል፥ ዓለም እየሔደችበት ያለውን የቴክኖሎጂ ልህቀት፣ ፍጥነት እና የጉዳዩን ምጣኔ ሀብታዊ ዳፋ መገንዘብ አለበት፤ ሲሉም አሳስበዋል፡፡
ልዩ ልዩ መንግሥታዊ ያልኾኑ የሲቪክ ተቋማት፣ መንግሥት፥ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት በማክበር፣ ተደራሽነታቸውን ያገዳቸውን ብዙኃን መገናኛዎች እንዲከፍት፣ በብዙኃን መገናኛ ገጾቻቸው አማካይነት ጥሪ እያደረጉ ሲኾን፣ በመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ፕሮግራም ዲሬክተር አቶ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ተቋማቸው፥ በጉዳዩ ላይ መፍትሔ እንዲመጣ፣ በቀጥታ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ብሎ ለሚያስበው፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቢሮ ደብዳቤ ማስገባቱን አስታውቀዋል።
ላለፉት ሦስት ዓመታት፣ የኢንተርኔት መቋረጥ፥ የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት እንደሚያባብስ፣ የተለያዩ አካላት፥ የሰብአዊ መብቶችን ጥሰት ለማስረዳት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ የጠቀሱት ዲሬክተሩ፣ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ሕክምናም ኾነ ሌሎች አገልግሎቶችን እንዳያገኙ እያደረገም እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ አቶ አጥናፍ አክለውም፣ “በቅርቡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና የትዊተር አካውንት፣ ከደንበኞች ጋራ ባደረገው ምልልስ፣ አላቋረጥንም ወይም የዘጋነው የማኅበራዊ ሚዲያ የለም፤ የሚል ምላሽ፣ ለአንድ ደንበኛቸው ሰጥተዋል፡፡ ከእነርሱ በላይ የኾነ አካል እንደሚያቋርጥ ይታወቃል፤” ብለዋል፡፡
የማኅበራዊ ብዙኃኑ መገናኛ መድረኮች እገዳ፣ እንዲሁም በዐማራ ክልል እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየታየ ያለው የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት አጋላጭ እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ የአሁኑ እገዳ፣ የሕግ ድጋፍ የሌለው፣ ግልጽ ተጠያቂ አካል ያልተቀመጠለት እንደኾነ በመጥቀስም ተችተዋል፡፡
በተመሳሳይ፣ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ኢትዮጵያ ማኅበር ዲሬክተር አቶ ባሕሩ ዘይኑ፣ ማኅበራቸው፣ በኢመደበኛ መልኩ፣ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ብሎ ላመነባቸው ተቋማት ጥያቄ እንዳቀረበ ገልጸው፣ ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ፣ ምላሽ ማጣቱ ተገቢ እንዳልኾነ ወቅሰዋል።
ማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎቹ ለምን ተዘጉ? መቼስ ይከፈታሉ? የሚለውን ለመረዳት፣ የአሜሪካ ድምፅ፣ የኢትዮ ቴሌኮምን ምላሽ በተደጋጋሚ ለማግኘት ቢሞክርም፣ በአጭር የዋትስአፕ የጽሑፍ መልዕክት፣ የመዝጋቱ ውሳኔ፣ የተቋሙ አለመኾኑን በመግለጽ፣ ሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናትን አነጋግሩ፤ የሚል ምላሽ አግኝቷል።
ይኹን እንጂ ተቋማችን፣ ባለፈው አንድ ወር እና ከዚያ በላይ፣ ለጥያቄአችን በሓላፊነት ምላሽ የሚሰጥ የመንግሥት አካል ሳያገኝ ቀርቷል። በአገሪቱ የቴሌኮም ሥራዎችን ለመሥራት፣ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ሥራ የገባውም ሳፋሪ ኮም፣ ለአራት ወራት በዘለቀው፣ በዚኹ የማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ እገዳ፣ የደረሰበት ጉዳት አሊያም ኪሳራ ካለ እንዲያስረዳ፣ በተደጋጋሚ ለቃለ መጠየቅ ቢጋበዝም፣ ፈቃደኛ ሳይኾን ቀርቷል።