ምስራቃዊውን የኮንጎ ትልቅ ከተማ የተቆጣጠሩት በሩዋንዳ የሚደገፉ አማፂያን፣ ዋና ከተማውን ኪንሻን እስከሚቆጣጠሩ ድረስ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ሐሙስ እለት አስታውቀዋል። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኬዲ በበኩላቸው አማፂያኑን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ወታደራዊ ቅስቀሳ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የመከላከያ ሚንስትራቸውም ለውይይት የቀረበውን ጥሪ ውድቅ አድርገዋል።
የኮንጎ መከላከያ ሚኒስትር ጋይ ካቦምቦ ሙአዲያምቪታ በቪዲዮ አማካኝነት ባስስተላለፉት መልዕክት፣ ውይይት ለማድረግ የሚደረግ ማንኛውም እቅድ "ወዲያውኑ እንዲከሽፍ ይደረጋል" ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ የቅርብ አጋር የሆኑት ሙአዲያምቪታ በዚሁ መልዕክታቸው "እዚሁ ኮንጎ ቆይተን እንዋጋለን። እዚህ በህይወት መኖር ካልቻልን ደግሞ፣ እዚሁ እንሞታለን" ብለዋል።
የኤም 23 አማፂያን በበኩላቸው ከመንግስት ጋራ ንግግር ለመጀመር ፈቃደኛ መሆናቸውን የተናገሩ ቢሆንም፣ ዓላማቸው ግን የፖለቲካ ስልጣን ለማግኘት መሆኑን ከቡድኑ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ኮርኔል ናንጋአ ገልፀዋል። "ወደ ኪንሻሳ ሄደን ስልጣን መረከብ እና አገሪቱን መምራት እንፈልጋለን" ያሉት ናንጋአ፣ 1ሺህ 500 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ዋና ከተማ እንዴት ለመግፋት እንዳሰቡ የገለጹት ነገር የለም።
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፓል ካጋሜ በኮንጎ ጉዳይ ከአንጎላ አቻቸው ጃአዎ ሎሬንኮ ጋራ መነጋገራቸውን አመልክተዋል። ሎሬንኮ ግጭቱ እንዲቆም ለማሸማገል እየሞከሩ ሲሆን፣ ከአንድ ቀን በፊት ከፕሬዝደንት ቲሺሴኬዲ ጋራ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
መድረክ / ፎረም