ሩሲያ ትላንት ቅዳሜ የካቲት 29 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በዩክሬን ምሥራቃዊ ከተማ ዶቭሮፒሊያ ላይ በአንድ ምሽት ባደረሰችው፣ የሚሳዬልና ሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ቢያንስ 11 ሰዎች ሲገደሉ፣ አምስት ሕፃናትን ጨምሮ 30 ሰዎች መቁሰላቸውን የዩክሬን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሰሜን ምስራቅ ካርኪቭ ግዛት ላይ በደረሰው ጥቃት ፣ ሌሎች ሦስት ሰላማዊ ሰዎች መሞታቸውን ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል። የሩሲያ ጦር ኃይል ወደ ይክሬኗ ከተማ፣ ባስወነጨፋቸው ባላስቲክ ሚሳዬሎች፣ በተኮሰቸው በበርካታ ሮኬቶች እና በላከቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት፣ ዶቭሮፒሊያ ውስጥ የሚገኙ ስምንት የተለያዩ ሕንፃዎችና 30 መኪኖች መውደማቸውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ፣ በቴሌግራም መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ ላይ እንዳሰፈሩት፣ "በጥቃቱ ምክኒያት የተቀጣጠለውን እሳት ለማጥፋት ርብርብ እየተደረገ በነበረበት ወቅት፣ ሌላ ተጨማሪ ጥቃት ደርሶ የእሳት አደጋ መከላከያ እና ማጥፊያ መኪናውን ላይ ጉዳት አድርሷል" ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በቴሌግራም መልዕክታቸው፣ በከፊል የወደሙ ፍርስራሾችን፣ በእሳት ውስጥ የተዋጡ ሕንፃዎችን እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ከሕንፃዎቹ ላይ ፍርስራሾችን ሲያነሱ የሚያሳዩ ምስሎችን አጋርተዋል።
ከዩክሬን የዶኔትስክ ግዛት የፖክሮቭስክ ቁልፍ ማዕከል 22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዶቭሮፒሊያ፣ ከጦሩነቱ በፊት ወደ 28 ሺሕ የሚጠጉ ነዋሪዎች ያሉባት ከተማ ስትኾን ፣ የሩስያ ወታደሮች ለሳምንታት ጥቃት ሲሰነዝሩበት መቆየታቸውን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ አያይዘው፣ ካርኪቭ ላይ በተፈጸመ ሌላ የድሮን ጥቃት፣ ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች ሰባት ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል። የዩክሬ ጦር በበኩሉ፣ ሩሲያ 145 ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሦስት የተለያዩ ሚሳዬሎችን ልካ ጥቃቱን እንደፈጸመች አስታውቋል።
የጦር ኃይሉ አክሎም፣ አንድ የክሩዝ ሚሳዬል እና 79 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መቶ መጣሉን ገልጿል። ሌሎች 54 ሰው አልባ አውሮፕላኖች ደግሞ በኤሌክትሮኒካዊ መንገድ በተወሰዱ የመከላከያ ርምጃዎች ምክንያት ዒላማቸው ላይ ሳይደርሱ እንዲከሽፉ መደረጋቸውን የዩክሬን ወታደራዊ ክንፍ አስታውቋል።
መድረክ / ፎረም