‘መልካምነት እና ርህራሄ የታከለበት ሕክምና ለህመምተኛው ረዥም እና ጤናማ ህይወት ማስገኘት ብቻ ሳይሆን፤ ለጤና አጠባበቅ ባለሙያው ለራሱ ጭምር ሁነኛ ጥቅም የሚቸር ልዩ መድሃኒት ነው’ ይላል፤ የጤና ክብካቤን ጥራት እና ፋይዳ የፈተሸ አንድ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለንባብ የበቃ መጽሃፍ። ‘ርህራሄ ስለ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ተአምራዊ ፈውስ ሊታይም ይችላል’ ይላል።
‘ኮምፓሽኖሚክስ’ በሚል ርዕስ የምርምር እና የሕክምና ባለሞያዎቹ ዶ/ር ስቲፈን ትሪሲያክ እና ዶ/ር አንተኒ ማሰሬሊ በጋራ የጻፉት ይህ መጽሃፍ፡ ሕሙማንን በርህራሄ ማከም የሚያስገኛቸውን ተጨባጭ ጠቀሜታዎች የሚያመላክቱ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ያቀርባል።
“አንድ ሐኪም ለታካሚዎቹ ርህራሄ በሚያሳይበት እና የህክምና አገልግሎቱ ርህራሄ በታከለበት አቀራረብ በመመራቱ ብቻ፣ ሕሙማኑ በተሻለ ፈጥነው እንዲፈወሱ የሚያግዝ አንዳች ለየት ያለ ነገር የመከሰቱን እና በአንጻሩም ሃኪሙ ራሱ ይበልጥ ደስተኛ ከመሆኑም ባሻገር፣ የብዙዎችን ስቃይ በማየት ለህመም የመዳረግ እድሉም የሚቀንስበትን ምስጢር ይተነትናል።
ይህን መሰል የሕክምና አገልግሎት አቀራረብ ዘይቤ በመላበስ ለዚህ አይነተኛ ሞያዊ ማንነት የቀረበ ህይወት መርጣ የኖረች እና ያለፈች ናት፥ በዚህ ቅንብር ህይወት እና ሥራዋን የምንዘከራት ባለታሪክ፣ በቅርቡ በድንገተኛ ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ዶ/ር አደይ ጸጋዬ ገብረመድህን።
የኒው ዮርክ ከተማ በኮቪድ ወረርሽኝ ክፉኛ በተመታችበት ወቅት ታገለግልበት በነበረው የሴንት ባርናባስ ሆስፒታል ትመራው በነበረው የጽኑ ሕሙማን መርጃ ክፍል ያሳየችው ብቃት እና ርህራሄ በኒው ዮርክ ታይምስ እና በዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጦች፤ እንዲሁም በታዋቂ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች ጭምር ተዘግቧል።
መድረክ / ፎረም