በግጭት የሚታመሰውን ምሥራቃዊ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ለማረጋጋት የተሰማራው ቀጣናዊ ወታደራዊ ኃይል፣ በአጎራባች አገሮች ላይ ያለውን ጥርጣሬ አሰማ፡፡
እአአ በ1990ዎቹ እና በ2000ዎቹ ዓመታት፣ በማዕከላዊ አፍሪካ የነበሩትን ጦርነቶች ተከትሎ፣ በአሁኑ ወቅት ምሥራቅ ኮንጎ፣ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች የሚተራመሱባት ኾናለች፡፡ ድምፁን አጥፍቶ የቆየው ኤም23 የተባለው ቡድን፣ እአአ በ2021 ብቅ ብሎ፣ ብዙ ጥፋት እያደረሰ ነው፡፡ በሩዋንዳ ይደገፋሉ የሚባሉት ታጣቂዎቹ፣ የሰሜናዊ ኪቩ ክፍለ ግዛት ሰፊ አካባቢዎችን የተቆጣጠሩ ሲኾን፣ በብዙ መቶ ሺሕ ነዋሪዎችን አፈናቅለዋል፡፡
ሰባት አባል ሀገራት ያሉት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ፣ የምሥራቅ ኮንጎን ሁከት የሚያረጋጋ ወታደራዊ ኃይል ለማቋቋም የወሰነው፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ውስጥ ሲኾን፣ የኬኒያ ወታደሮች በኅዳር ወር፣ በቅርቡ ደግሞ የቡሩንዲ እና የደቡብ ሱዳን ወታደሮች ገብተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት፣ የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ በሰጡት ቃል፣ “የአገራችን ኃይል ገለልተኛ ስለኾነ፣ ከኤም23 ጋራ አይዋጋም፤” ብለዋል፡፡
ባዕዳኑን ወታደሮች በተለይም የዩጋንዳን ኃይሎችን በሚመለከት፣ ኮንጎ ውስጥ፣ አንዳንድ ወገኖች ጥርጣሬ እንዳላቸው እየተናገሩ ነው፡፡ ዩጋንዳ፣ በምሥራቅ ኮንጎ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ታሪክ ያላት ሲኾን፣ ከኤም23 ቡድን ጋራ በተያያዘም፣ ብዙዎች ጥርጣሬ እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡
ጉዳዩን እንዲከታተል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመደበው ነፃ የባለሞያዎች ቡድን፣ የዩጋንዳ መንግሥት የኤም23 ታጣቂዎች፣ በዩጋንዳ እና በኮንጎ ድንበር ሲወጡ እና ሲገቡ እያየ እንዳላየ እየኾነ ነው፤ ሲሉ አሳውቀዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ኃይሎችን የሚመለከት ስጋት ስለ መኖሩ ያመኑት የኮንጎ መንግሥት ቃል አቀባይ፣ “ኾኖም፣ ወታደሮቹ የገቡት፣ ቀውሱን ለማብረድ በአገራችን መንግሥት ተጋብዘው ነው፤” ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ኮንጎ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎችም ምዕራባውያን ሀገራት እንዲሁም፣ ነፃው የመንግሥታቱ ድርጅት የባለሞያዎች ቡድን፣ “ሩዋንዳ ኤም23ን ትረዳለች፤” ብለው ይወነጅሏታል፡፡ ኪጋሊ ግን ክሡን ታስተባብላለች፡፡
ምሥራቅ ኮንጎ ውስጥ፣ “ለተገፉ ማኅበረሰቦች እታገላለኹ፤” የሚለው ኤም23፣ ከመንግሥቱ ጋራ ለመደራደር ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡