በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የርዕዮት ዓለሙ ይግባኝ ውድቅ መደረጉን ዓለምአቀፍ ድርጅቶች አወገዙ


ርዕዮት ዓለሙ
ርዕዮት ዓለሙ

በጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ላይ የበታች ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማፅናቱ ያሣዘናቸው መሆኑን ዓለምአቀፉ የሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት - IWMF እና ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት - ሲፒጄ አስታውቀዋል፡፡

please wait

No media source currently available

0:00 0:03:07 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

በጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ላይ የበታች ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማፅናቱ ያሣዘናቸው መሆኑን ዓለምአቀፉ የሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት - IWMF እና ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት - ሲፒጄ አስታውቀዋል፡፡
የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት - ሲፒጄ
የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት - ሲፒጄ

IWMF መግለጫውን በይፋ አውጥቶ ያሠራጨ ሲሆን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኤሊሣ ሊዝ ሙኞዝ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሃሣብን የመግለፅ ነፃነት ጉዳይ ድርጅታቸውን በእጅጉ የሚያሠጋው መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ዓለምአቀፍ የሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት
ዓለምአቀፍ የሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ድርጅት

“ርዕዮት ለጋዜጠኝነት ነፃነት ያላትን ድፍረት፣ ቁርጠኝነትና ጥንካሬ እናደንቃለን፡፡ ቀደም ፀሰል የተላለፈባት ፍርድ በመፅናቱ ማዘናችንን እንገልፃለን፡፡ ይህ ለእርሷ ሕይወት ብቻ ሣይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሣብን በነፃነት ለመግለፅ ነፃነትም ጭምር አሣዛኝ ቀን ነው፡፡ ለሌሎች በእሥር ላይ ለሚገኙ ጋዜጠኞችም የሚሰማንን መቆርቆር እንገልፃለን” ብለዋል ዳይሬክተሯ፡፡

ኤሊሣ ሊዝ ሙኞዝ - ዋና ዳይሬክተር - IWWF
ኤሊሣ ሊዝ ሙኞዝ - ዋና ዳይሬክተር - IWWF
ዓለምአቀፉ የሴቶች የመገናኛ ብዙኃን ባወጣው ይፋ መግለጫው ኢትዮጵያ ውስጥ እሥር ቤት ውስጥ ባሉ ጋዜጠኞች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ፣ በፕሬስ ነፃነት አያያዟ በዓለም እጅግ ጨቋኝ ከሚባሉ ሃገሮች ተርታ መመደቧን አስታውሶ ባለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን በአፍሪካ ውስጥ ከኤርትራ በስተቀር ሌላ ማንም ሃገር በማይስተካከለው ሁኔታ ጋዜጠኞችን ማሠሩን አመልክቷል፡፡

“የሚወቅሱትን ድምፆች ለማፈን በአደናጋሪው የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ሕግ መንግሥቱ በተደጋጋሚ መጠቀሙ እጅግ አሣሣቢ ነው” ያለው ይኸው መግለጫ ርዕዮት በሰኔ 2003 ዓ.ም (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ከተያዘች ወዲህ ለብዙ ወራት ያለ ክሥ መታሠሯን እና በኋላም ተግባሯ ሙሉ በሙሉ የጋዜጠኛ ሥራ ሆኖ ሣለ በሽብር ፈጠራ መከሰሷን ዘርዝሯል፡፡

“ባለፈው ነሐሴ በከፊል በተሣካው ይግባኝ በርዕዮት ላይ ቀድሞ የተላለፈው የ14 ዓመት እሥራት ፍርድ ወደ አምስት ዓመት እንዲቀንስ ቢደረግም እስከአሁን የቆየችባቸው 19 ወራት እያንዳንዷ ቀን ወይም ወደፊት በእሥር የምትቆይባቸው 41 ወራት እያንዳንዷ ቀን የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሬስ ነፃነትን ዋጋ እንዳረዳ የምትጎተጉት ማስተወሻ ነች” ብሏል መግለጫው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ ውሣኔውን እንደሚቃወምና እንደሚያወግዝ የአፍሪካ የአድቮኬሲ አስተባባሪ መሐመድ ኬይታ አስታውቋል፡፡
መሐመድ ኬይታ - የአፍሪካ የአድቮኬሲ አስተባባሪ - ሲፒጄ
መሐመድ ኬይታ - የአፍሪካ የአድቮኬሲ አስተባባሪ - ሲፒጄ

“ያሣዝናል - አለ ኬይታ - ኢትዮጵያ ውስጥ ለሕግ የበላይነት መከበር ቀኑ የኀዘን ቀን ነው፡፡ ምክንያቱም በርዕዮት ዓለሙ ላይ የተመሠረተቱት የሽብር ፈጠራ ክሦች በማስረጃ ለማስደገፍ የቀረቡት ፍፁም አስቂኝ ናቸው፡፡ እነዚህን ክሦች ፈትሸናቸዋል፡፡ የተከሠሠችው በጋዜጠኝነት ላከናወነቻቸው ሥራዎች ነው፡፡ እነዚህ ተቀባይነት ያላቸውና ሕጋዊም መረጃን የመሰብሰብና የማሠራጨት ሥራዎቿ መንግሥትን የሚወቅሱ ናቸው፣ የተቃዋሚ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በተመለከተም ዘግባለች፡፡ ይህ መንግሥቱን የሚተቹ የግርግዳ ላይ ፅሁፍ ሣይቀር እንደማስረጃ የቀረበበት ክስ አስገራሚ ነው፡፡” ብሎታል፡፡

በክሦቹ ላይ የተጠቀሱት ጭብጦች በማንም ነፃ ወገን እንደሽብር ፈጠራ አድራጎት ማረጋገጫ አለማግኘታቸውን ወይም አለመደገፋቸውን የሲፒጄው አስተባባሪ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የታየው “የፍትሕ መጨናገፍ ነው” ብሎታል፡፡

ሃገሪቱ ለሽብር ፈጠራ አድራጎት የተጋለጠች መሆኗንና መንግሥቷም የበረታ የሽብር ፈጠራ እንቅስቃሴዎች ሥጋት እንዳለበት ሲፒጄ እንደሚገነዘብ ሞሐመድ ኬይታ አመልክቶ “የጋዜጠኝነት ሥራቸውን በሚያከናውኑ ባለሙያዎች ላይ የሽብር ፈጠራ ክሥ እየመሠረተ ሽብር ፈጠራን ከእውነተኛው መገለጫው እያሣሣተና ክብደቱንም እያቀለለው ነው” ብሏል፡፡

“በዚህ አድራጎቱ ርዕዮትና ባልደረቦቿ ዓለምአቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ እያደረገና የመናገር ነፃነትን ለማፈን እያደረገ ያለውን ተግባር እያጋለጠ ዋጋውን እራሱ ይከፍላል” ብሏል የሲፒጄው የአፍሪካ አድቮኬሲ አስተባባሪ ሞሐመድ ኬይታ፡፡

ርዕዮት ዓለሙ የዓለምአቀፉ የሴቶች ሚድያ ድርጅት የ2012 ዓ.ም በጋዜጠኝነት ላሣየችው ድፍረት እና የዚሁ የ2012 ዓ.ም የሄልማን/ሃሜት ሽልማቶች ተሸላሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡
XS
SM
MD
LG