በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫው አይደገምም አለ


መድረክና መኢአድ ቦርዱ ለአቤቱታቸው የሰተው ምላሽ በቂ አይደለም ይላሉ

የግንቦት 15ኡን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ መግለጫ የሰጡት ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫው እንዲደገም መጠየቃቸው፣ ይሄንኑ አቤቱታም ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማስገባታቸው ይታወሳል።

ይህንንም አስመልክቶ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መድረክና መኢአድ ያቀረቡት አቤቱታ በምርጫው ውጤት ህጋዊነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መረጃ የቀረበበት አይደለም ሲል አስታውቋል። ፓርቲዎቹ ምርጫው እንዲደገም ያቀረቡት ጥያቄም ተቀባይነት አለማግኘቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24, 2002 ለነዚሁ አቤቱታዎች ለመድረክ 16 ገጽ ለመኢአድ ደግሞ 14 ገጽ የሞላ የምላሽ ደብዳቤ በመጻፍ መልሷል። መድረክና መኢአድ ያቀረቡት አቤቱታ በምርጫ ውጤቱ ህጋዊነት ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መረጃ አልቀረበበትም ያሉት አቶ ተስፋዬ ለነዚሁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሰጡትን 30 ተጨማሪ የእጩ ማስመዝገቢያ ቀናቶች ጠቅሰው የምርጫ ቦርዱ “ለሁሉም ፓርቲዎች እኩል እድል” እንደሰጠ ገልጸዋል።

የመድረክ ሊቀመንበር ፕርፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለቪኦኤ በሰጡት አስተያየት ምንም እንኳን ፓርቲያቸው ላቀረባቸው 16 ነጥቦች ቦርዱ 16 ገጽ የሚሆን ምላሽ ቢሰጣቸውም፣ ምላሹ ለጉዳዩ የማይመጥንና እንደውም “ለዚህ ጉዳይ ክብደት የማይሰጥ አካል ድርሰት እንደጻፈ” ያህል እንደሚያዩት ገልጸዋል።

ቦርዱ ነጥብ በነጥብ የሰጣቸው ምላሾች አሳማኝና ትክክለኛ አለመሆናቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ መድረኩ ተጨማሪ መረጃ ለማቅረብ ዝግጁ እንደነበር በቅሬታ ደብዳቤው ላይ መግለጹንም ጠቅሰዋል።

ቀጣይ እርምጃ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ሊሆን እንደሚችል አስታውቀው ፕርፌሰር በየነ መድረኩ በጉዳዩ ላይ ዛሬ እንደሚወያይም አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG