የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሃገራቸውን ሁኔታ የሚገልፀውን፣ የወደፊት አቅጣጫና የራሣቸውንም ራዕይ የሚያመላክተውን የሁለተኛውን የሥልጣን ዘመናቸውን የመጀመሪያ ንግግራቸውን ለተወካዮች ምክር ቤቱ ጥምር ስብሰባ አደረጉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሪፐብሊካን ፓርቲው ተወካይ የሆኑት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ አባል ማርኮ ሩቢዮ የፓርቲያቸውን ምላሽ ከፕሬዚዳንቱ ንግግር ተከትለው በእንግሊዝኛና በስፓኝ ቋንቋ አሰምተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን የጀመሩት በዚህ ዓመት የሚናገሩለት ብዙ ስኬት መኖሩን ገልፀው ሲሆን በውጭ የሚገኙ ወታደሮቻቸው ከአሥር ዓመታት “አድቃቂ ጦርነት”እየተመለሱ መሆኑን በማብሰር ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ አክለውም ሃገራቸው ሁሉም ልጆች በደስታ የሚኖሩባት መሆን እንዳለባት አመልክተዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ኢኮኖሚ እየተነሣ መሆኑን፣ የቤቶች ዋጋ እየተሻሻለ መሆኑን የገለፁት ፕሬዚዳንት ኦባማ ብዙ ዜጎቻቸው ገና ኑሯቸውን ለማሸነፍ እየታገሉ መሆኑን ጠቁመው የሕዝብ ተወካዮች ከየፓርቲያቸው ጥቅሞች የሃገራቸውንና የሕዝባቸውን ጥቅም እንዲያስቀድሙ ከንግግራቸው መነሻ ጠይቀዋል፡፡
ብዙ ካስከፈለ የምጣኔ ኃብት ድቀት በኋላ ከስድስት ሚሊየን በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው “አሁን ብዙ አሜሪካዊያን የአሜሪካ መኪኖችን እየገዙ፣ ያነሰ የውጭ ነዳጅ እየተጠቀሙ ነው” ብለዋል፡፡
“አሁን ሃገራችን የምትገኝበት ሁኔታ - አሉ ፕሬዚዳንቱ በተሻለ ሁኔታ ጠንካራ ሲሆን ቀውሱ የጣለብንን ፍርስራሽ አፅድተናል፡፡”
ይሁን እንጂ ብዙ አሜካዊያን አሁንም የሙሉ ጊዜ ወይም ቋሚ ሥራ እየፈለጉ ባሉበት፣ የሠራተኞች ደመወዝ እጅግ አንገራጋሪና ደካማ በሆነበት ሁኔታ የግዙፎቹ የንግድ ድርጅቶች ትርፍ ግን እስከዛሬ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ማሻቀቡን አመልክተዋል፡፡
የዚህ ትውልድ ተልዕኮ የአሜሪካን የምጣኔ ዕድገት ማቀጣጠል እና እየተነሣ ያለውን ታታሪ መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በመጠን ማሣደግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
“ችሎታ ያላቸውን በፈጠራ የታደሉትንና ለማደግ እየተፍጨረጨሩ ያሉትን ከውጭ የመጡ ሰዎችን በብዛት በሣብን መጠን ኢኮኖሚያችን እየጠነከረ ነው፤ እናም አጠቃላይ የኢሚግሬሽን ማሻሻያ የምናደርግበት፣ የምንጨርስበት ጊዜው አሁን በመሆኑ ላይ የቢዝነሱ፣ የሠራተኛው፣ የሕግ ማስከበር፣ የዕምነት ማኅበረሰቦች መሪዎች ተስማምተዋል፡፡ ይህንን ሥራ አሁን መጨረስ አለብን” ብለዋል ፕሬዚዳንት ኦባማ፡፡
“ይህቺ ሃገር የተገነባችበትን መሠረት ገና ያላለቀ ግዴታ መቀጠል አለብን፤ ይህም ከየትም ና፣ ምንም ምሰል፣ ማንንም ውደድ በርትተህ ከሠራህና ኃላፊነቶችህን ከተወጣህ ወደፊት እንደምትራመድ የሚናገር ሃሣብ ነው፡፡” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ይህ “ገና ያላለቀ” ያሉት ግዴታ መንግሥት በብዙዎች ስም እንደሚንቀሣቀስ፣ ነፃ ፈጠራን የሚያበረታታ፣ የግል ተነሣሽነትን የሚሸልም፣ ለእያንዳንዱ ሕፃን የዕድል በሮችን የሚከፍት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሥራው መጀመር ያለበት በሃገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ ትልቅ ትርጉም ያለውን የበጀቱን መሠረታዊ ውሣኔዎች ማሣለፍ እንደሆነ ከፓርቲ ጉዳይ የሃገርን ጥቅም እንዲያስቀድሙ ደግመው የጠየቋቸውን የሕዝብ ተወካዮች አሣስበዋል፡፡
“የሃገሪቱን የበጀት ጉድለት ለማካካስ ጭነቱን እንዲሸከሙ አረጋዊያንና በሥራ የሚታትሩ ቤተሰቦች -መጠየቅ የለባቸውም” ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ መሠረተ-ሠፊ የሆነ የምጣኔ ኃብት ዕድገት እያንዳንዱ የሚገባውን ድርሻውን ይወጣ ዘንድ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል፡፡
የሥራ ፈጠራን የሚያበረታታና የሃገሪቱንም ዕዳና የበጀት ጉድለት መቀነስ የሚያስችል የግብር ማሻሻያ ለማውጣት ፓርቲዎቹ በጋራ መሥራት የሚችሉበት ጊዜው አሁን መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ “ከበርቴዎቹ የሚከፍሉት ታክስ በብርታት ከሚታትሩት ሠራተኞቻቸው ያነሰ ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡
የግብር ማሻሻያና የማኅበራዊ ጥቅሞች ማሻሻያ ለሁለቱም ወገኖች ከባድ እንዲሆኑ የሚያደርግ ፖለቲካ የመኖሩን ጉዳይ እንደሚገነዘቡ የገለፁት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሥራ ዕድሎች መጥፋትን፣ የምጣኔ ኃብቱን መጎዳትና በታታሪ አሜሪካዊያን ላይ የሕይወት ሸክሞችን ማብዛትን ከሚያስከፍል አማራጭ ይልቅ ወደ መቻቻል እንዲገቡ መክረዋል፡፡
እርሣቸው ያዘጋጁት አዲስ ዕቅድ በወጭ እራሱን ሙሉ በሙሉ የሚችል፣ ሪፐብሊካኖቹና ዴሞክራቶቹ ከ18 ወራት በፊት ከተስማሙበት የበጀት ማዕቀፍ ጋር የሚጣጠም መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በኃይል አቅርቦት በኩልም ሃገራቸው ዛሬ የዛሬ 15 ዓመት ከነበረው ይበልጥ ነዳጅ እራሷ እያወጣች መሆኑን ሚስተር ኦባማ ጠቁመው የተፈጥሮ ጋዝ ምርት እስከአሁን ታይቶ በማይታወቅ መጠን ማደጉን፣ ተሽከርካሪዎችም የነዳጅ አጠቃቀማቸው በግማሽ መቀነሱን ገልፀዋል፡፡ በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን የፀሐይና የነፋስ ኃይልን በመሣሰሉ ታዳሽ ኢነርጂ ምንጮች ላይ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
አማቂ ጋዞችን ወደአካባቢ የሚያስገቡ ውጤቶች መቀነስ እንዳለ ሆኖ የአየር ንብረት ለውጡን ለመዋጋት የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲኖሩ ያሳሰቡት ኦባማ የሃገራቸው ምጣኔ ኃብት ሳይጎዳ ትርጉም ያለው እርምጃ ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
ለአየር ንብረት ለውጡ ሁለቱም ፓርቲዎች በገበያ ላይ የተመሠረተ መፍትሔ እንዲያበጁ ጠይቀው የተወካዮች ምክር ቤቱ የወደፊት ትውልዶችን ከአደጋ ለመጠበቅ የማይሠራ ከሆነ እራሣቸው በሥልጣናቸው ሊያሣልፏቸው የሚችሉ ውሣኔዎችን እንደሚያወጡ ተናግረዋል፡፡
በመሠረተ ልማት በኩልም በሃገራቸው ውስጥ ወደ ሰባ ሺህ የሚጠጉ የመዋቅር ችግር ያለባቸው ድልድዮችና ሌሎችም በአስቸኳይ እንዲጠገኑ የሚያስችል መርኃግብር ሃሣብ አቅርበዋል፡፡
“አሜሪካን መልሶ የመገንባት አጋርነት” የሚባል ሃሣብም ፕሬዚዳንቱ ያቀረቡ ሲሆን ይህ ሃሣባቸው ሸቀጦችን ለማንቀሣቀስ የሚያስችሉ ዘመናዊ ወደቦችን ለመገንባት፣ ማዕበልን መቋቋም የሚችሉ የቱቦ መሥመሮችን ለመዘርጋት፣ ለሕፃናቱን አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን ለማነፅ የግሉን ዘርፍ መሣብ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
State Of The Union Address
የቤቶች ዋጋ በ2007 ዓ.ም ገብቶ ከነበረበት ውድቀት በፍጥነት እያገገመ መሆኑንና የቤቶች ሽያጭ መጠንም በሃምሣ ከመቶ መጨመሩን ፕሬዚዳንቱ ገልፀው ኮንግረሱ ግዴታዎቻቸውን በኃላፊነት የሚወጡ የቤት ባለቤቶች በዓመት እስከ ሦስት ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ማዳን እንዲችሉ የሚያደርግ ሕግ እንዲያወጣ አሳስበዋል፡፡በትምህርት በኩልም ከትምህርት ቤት ዕድሜ በፊት ላለው የሕፃንነት ጊዜ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አመልክተው ሕፃናት በዚያ ጊዜ የሚያገኙት ትምህርት ከፍተኛ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት የሚጨርሱ ተማሪዎች ቁጥር በብዙ እንዲጨምር፣ ለአቅመ ሄዋን ያላደረሱ ልጃገረዶች እርግዝና እንዲቀንስ እና አመፀኛ ወንጀል መጠንም እንዲወርድ ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በውጭ የሚገኝ የአሜሪካ ጦርን በተመለከተው የንግግራቸው ክፍል አፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኙ 34 ሺህ ወታደሮቻቸው በያዝነው የአውሮፓዊያን ዓመት ውስጥ እንደሚመለሱ ገልፀዋል፡፡
“አልቃልዳ አሁን የራሱ የቀድሞ ጥላ ነው፤ ዩናይትድ ስቴትስ ግን በየአቅጣጫው የሚረጨውን ተኩሱን ስጋት ለመጋፈጥ በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ አሜሪካዊያንን ባሕርማዶ መላክ አይኖርባትም” ብለዋል፡፡
“ይልቅ - አሉ ፕሬዚዳንቱ - ዩናይትድ ስቴትስ እንደ የመን፣ ሊብያ፣ ሶማሊያ ያሉትን ሃገሮች የራሣቸውን ደህንነት እንዲጠብቁ ማገዝ፣ አስፈላጊ ሲሆንም አሜሪካን በሚያሠጓት ሽብርተኞች ላይ ቀጥተኛ እርምጃ መውሰድ የሚያስችላቸው አቅም እንዲኖራቸው ማስቻል ይገባል፡፡”
አሜሪካ እጅግ በፈጠነ ሁኔታ እያደገ የጣውን የኢንተርኔት ጥቃት ሥጋት መጋፈጥ እንደሚኖርባት ፕሬዚዳንቱ አሳስበው የኢንተርኔት አድፋጭ ጠልቆ ገቦች የግለሰቦችን የግል መረጃና ማንነት እንደሚሰርቁ፣ የግል የኢሜል መልዕክቶችን እንደሚበረብሩ ሌሎች መንግሥታትና ኩባንያዎች የግዙፍ የንግድ ኮርፐሬሽኖችን ምሥጢሮች እንደሚዘርፉ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ጠላቶችም የሃገሪቱን የኃይል ማመንጫና ሥርጭት መረብ፣ የፋይናንስ ተቋማትን እና የአየር ትራፊክ ቁጥጥር ሥርዓቱን ለማወክ የሚያስችላቸውን አቅም ለማግኘት እየጣሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢንተርኔት ደህንነት ወይም ሳይበር መከላከያን ማጠናከር የሚያስችል ትዕዛዝ በቅርቡ ፈርመው ማውጣታቸውንም አስታውቀው መንግሥቱ የኢንተርኔት መረቦችን ከአደጋ መጠበቅ እና ጥቃቶችንም ማስቆም የሚያስችለውን አቅም የተወካዮች ምክር ቤቱ እንዲሰጠው ጠይቀዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
“እጅግ በደኸዩት ሃገሮች ውስጥ እየታየ ያለው ዕድገት ሁሉንም ያሻሽላል” ብለዋል ሚስተር ኦባማ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ከአጋሮቿ ጋር ሆናም በመጭዎቹ ሃያ ዓመታት ውስጥ የበረታና ሥር የሰደደ ድኽነትን ለማጥፋት እንደምትሠራና መጭው ትውልድም ከኤድስ ነፃ የሆነ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡
“በዚህ የታሪካዊ ለውጥ ጊዜ - አሉ ፕሬዚዳንት ኦባማ - ነፃነትን ለሚሹ ሁሉ ዩናይትድ ስቴትስ ቀንዲል መሆን አለባት፡፡”
“ዩናይትድ ስቴትስ ከአሜሪካዎቹ እስከ አፍሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ እስያ የጠንካራ ትብብሮች መልሕቅ ሆና ትቀጥላለች፡፡” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
ዩናይትድ ስቴትስና መካከለኛው ምሥራቅ ዜጎች ሁለንተናዊ መብቶቻቸውን በጠየቁ ጊዜ ሁሉ ወደ ዴሞክራሲ የተረጋጋ ሽግግር እንዲኖር እንደሚደግፉ ፕሬዚዳንት ኦባማ አመልክተዋል፡፡
በሃገራቸው ውስጥም በአሁኑ ጊዜ እጅግ አንገብጋቢና አነጋጋሪ የሆነውን የጦር መሣሪያ በግል ይዞታነት የመገኘት ጉዳይንም አንስተው ኮንግረሱ የሃገሪቱ “እጅግ ውድ የሆነ ሃብት” ያሏቸውን ሕፃናትን ከአደጋ የሚጠብቅ ሕግ እንዲያወጣ ጠይቀው የሚወጣ ሕግም ግለሰቦች መሣሪያ ሲሸምቱ የቀደመ ማንነታቸው ላይ ፍተሻ እንዲደረግና የጦር ግንባር ዓይነት የጥቃት መሣሪያዎች ከከተሞች አውራ ጎዳናዎች ላይ እንዲወገዱ የሚደነግግ እንዲሆን አሳስበዋል፡፡
“በዓለም እጅግ ምርጡ” ያሉት የጦር ሠራዊታቸው አባላትምና ቤተሰቦቻቸው ባለተመሣሣይ ፆታ ግንኙነቶችን ጨምሮ የሚያገኙት ጥቅማጥቅም ሁሉ ያለአመሳሶ እንዲከበርላቸው ለማድረግ በመጣራቸው እንደሚቀጥሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረው አርበኞቿም በዓለም በከፍተኛ ደረጃ የሚገኝ እንክብካቤ፣ የአዕምሮ ጤና፣ ትምህርት፣ የሥራ ዕድሎችንና ጥቅሞችን ሁሉ እንዲያገኙ ሃገሪቱ ለእነርሱ መታመኗን እንደምታፀና አስታውቀዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአንድ ሰዓት ንግግር በተደጋጋሚና በተራዘሙ ጭብጨባዎች የታጀበ ነበር፡፡
ከፕሬዚዳንቱ ንግግር በኋላ የሪፐብሊካን ፓርቲውን ምላሽ በባለአሥራ አምስት ደቂቃ ንግግራቸው ያቀረቡት የፍሎሪዳው እንደራሴ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ማርኮ ሩቢዮ ያተኮሩት “በፌደራል መንግሥቱ ፖሊሲዎች ችሮታ የሚገኝ” ካሉት ምጣኔ ኃብት ይልቅ “ነፃና በራሱ የሚንቀሳቀስ ምጣኔ ኃብት” ይበልጥ ጠቃሚ መሆኑን በማስረገጥ ላይ ነው፡፡
የፕሬዚዳንት ኦባማ ፖሊሲዎች ግብር እንዲንር፣ ሥራም እንዲጠፋና ጥቅማጥቅሞች እንዲቀሩ በማድረግ መጤዎችን እንደሚጎዳ የተናገሩት ሴናተር ሩቢዮ የፕሬዚዳንቱን ፖሊሲዎች መቃወም ማለት ለበርቴዎች መቆም እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
“የምጣኔ ኃብት ዕድገት መካከለኛ ገቢ ያለውን አሜሪካዊ ለማገዝ እጅግ የተሻለው አማራጭ መሆኑን ያመለከቱት ሚስተር ሩቢዮ እንዲህ ዓይነቱ ዕድገት የሃገሪቱን ዕዳና የበጀት ጉድለት ለመቀነስ እንደሚረዳ ገልፀዋል፡፡ ታክስ መጨመር ለዚህ ዕድገት እንደማይጠቅም ሪፐብሊካኑ ሴናተር አመልክተው ሚስተር ኦባማ የሚያራምዱት “መፍትሔው ግብር አንሮ ብዙ የሚያወጣ መንግሥት ነው የማል የወደቀ ሃሣብ ነው” ብለዋል፡፡
ለአብነት ያነሱት የፕሬዚዳንቱ የጤና ጥበቃ ማሻሻያ “አነስተኛ ገቢ ላላቸው የታሰበ የሚባል ነገር ግን የሚጎዳቸው ነው” ብለዋል፡፡
ወደአሜሪካ እጅግ የተሻሉና እጅግ ብሩሕ የሆኑትን ለመሣብ ሕጋዊ የኢሚግሬሽን ሥርዓት የመኖርን ሃሣብ የደገፉት ሩቢዮ ሕገወጥ በሆነ ሁኔታ ሃገር ውስጥ የሚገኙትም የሚስተናገዱበት ኃላፊነት የተመላው አሠራር እንዲፈጠር አሳስበዋል፡፡
ሃገሪቱ ሁከትና አመፃን በተሣካ ሁኔታ መቆጣጠር እንደሚኖርባት እንደሚያምኑ ሴናተሩ አመልክተው ይህ ሲደረግ ግን የዜጎችን መሣሪያ የመያዝ ሕገመንግሥታዊ መብት የሚጋፋ በሆነ መንገድ መሆን እንደማይገባው ተናግረዋል፡፡
//የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን እና የሴናተር ማርኮ ሩቢዮን ንግግሮች ከተያያዙት የድምፅ ፋይሎች ያዳምጡ፡፡//