በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በመንግሥት የቀረበው የ28 ቢሊዮን ዶላር የጦርነት ኪሳራ “ገለልተኛ እይታ እንደሚያስፈልገው ባለሞያዎች ተናገሩ


በመንግሥት የቀረበው የ28 ቢሊዮን ዶላር የጦርነት ኪሳራ “ገለልተኛ እይታ እንደሚያስፈልገው ባለሞያዎች ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:37 0:00

በመንግሥት የቀረበው የ28 ቢሊዮን ዶላር የጦርነት ኪሳራ “ገለልተኛ እይታ እንደሚያስፈልገው ባለሞያዎች ተናገሩ

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ መነሻውን በትግራይ ክልል ባደረገው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የ28 ቢሊዮን ዶላር ወይም በወቅቱ ምንዛሪ ከ1ነጥብ5 ትሪሊዮን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን፣ ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በይፋ ባወጣው ዳሰሳዊ ጥናቱ አስታውቋል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ምሁራንና የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች፥ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፣ ዶ/ር ጉቱ ቴሶ እና አቶ እምነት ነጋሽ፣ ይፋ የተደረገው ጥናት፥ ተኣማኒነት እና ገለልተኝነት የጎደለው፣ ተጠያቂነትንም የማያመለክት እንደኾነ ተችተዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ባለፈው ግንቦት 9 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ የመሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት፣ ለሁለት ዓመት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የ28 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

በሚኒስትሩ ሪፖርት የተጠቀሰውን የጦርነት ኪሳራ መጠን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት፣ በዓለም ባንክ አማካሪነት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት የምጣኔ ሀብቱ ባለሞያ ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፣ “አገሪቱን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለ ጦርነት ነው፤" ይላሉ፡፡ ጦርነቱ ለወደፊትም ገና ትልቅ ዋጋ እንደሚያስከፍል ያመለከቱት ዶ/ር አክሎግ፣ አገሪቱ እስከ ዛሬ ታገኘው ከነበረው ገቢ ጋራ በማነጻጸር፣ የደረሰውን ጉዳት አብራርተዋል።

ይህ ጦርነት እስከ ዛሬ ከነበሩት ጦርነቶች የተለየ ነው፡፡ ከባዕድ አገር ጋራ ሳይኾን፣ ከአንድ ቋት ጥሪት ተካፍለው በተዋጉ የአንድ ሕዝብ ወገኖች መካከል የተደረገ ጦርነት እንደነበረ የሚገልጹት፣ የምጣኔ ሀብት ባለሞያው ዶ/ር ጉቱ ቴሶ ናቸው፡፡

“ይህ ጦርነት፣ "በዚያ ወቅት ያተረፍናቸውን ግኝቶች ሁሉ ይዞት ጠፋ፤"

ኢትዮጵያ፣ ባለፉት 15 ዓመታት፣ በተለይ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ መጠነኛ የኢኮኖሚ እመርታዎችን ያሳየችበት፣ የተወሰኑ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን በመክፈት፣ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብ የቻለችበት ወቅት እንደነበረ፣ ያወሱት ዶ/ር ጉቱ “ይህ ጦርነት፣ "በዚያ ወቅት ያተረፍናቸውን ግኝቶች ሁሉ ይዞት ጠፋ፤" ብለዋል።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፈሰር የነበሩትና በተለይም በትግራይ ክልል ላይ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን በሚያወጣው ቤልጅየም ገንት ዩኒቨርሲቲ፣ በምርምር ሥራ እና በሦስተኛ ዲግሪ ጥናት ላይ የሚገኙት አቶ እምነት ነጋሽ፣ የደረሰው ጉዳት፣ በገንዘብ እና በንብረት ውድመት ብቻ የሚተመን አለመኾኑን ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ተቋማቸው፥ መነሻውን በትግራይ ክልል ባደረገው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ የደረሰውን ጉዳት እና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት(Damage and Needs Assessment) በማከናወን፣ የጥናቱን ውጤት ለመንግሥት እንዳቀረበ መናገራቸውን፣ የአገር ውስጥ ብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡

አቶ እምነት ነጋሽ፣ በጦርነቱ ጉዳት መድረሱን ተቀብለው፣ ጥናቱ ግን፣ ታማኝነት የጎደለውና በገለልተኛ ወገን ያልተዘጋጀ መኾኑን በመጠቅስ ይከራከራሉ፡፡

ዶ/ር አክሎግ በበኩላቸው፣ ለዚኽ አውዳሚ ጦርነት የቁጥሩ መብዛት እና ማነስ ሳይኾን፣ ሓላፊነት እና ተጠያቂነት ያለበት ማን ነው? ብለን ልንጠይቅ ይገባል፤ ይላሉ፡፡ “ይህን ያህል ገንዘብ በጦርነቱ ካወጣን በኋላ፣ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ መጠየቃችን፣ ተመልሰን ወደዚያው ጦርነት ውስጥ ላለመግባታችን ዋስትናችን ምንድነው?” ብለው ይከራከራሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመቀልበስና ከጦርነት በፊት ወደነበረበት ኹኔታ ለመመለስ እንዲቻል፣ እ.ኤ.አ. ከ2023 እስከ 2028 ድረስ የሚቆይ፣ የአምስት ዓመታት የመልሶ ማቋቋም እና ግንባታ አገራዊ የዕቅድ ማኅቀፍ ማዘጋጀቱን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ፣ ለምክር ቤቱ የፕላን የበጀት እና የፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማስታወቃቸው

ተነግሯል። በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥም፣ የደረሰውን ጉዳት መጠንና የመልሶ ግንባታ ፍላጎት የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ሚኒስትሩ፣ በሰጡት መግለጫቸው ማመልከታቸው ተዘግቧል፡፡

/የባለሞያዎችን ሙሉ አስተያየት ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG