በመተንፈሻ አካላት ሕመም ሳቢያ ጥብቅ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ለሚገኙት የሮማ ካቶሊክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲንስ ፍራንሲስ ለመጸለይ ከዓለም ዙሪያ የተጓዙ፣ በርካታ ምእመናን ዛሬ ማክሰኞ ሮም በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ተሰባስበዋል።
ቫቲካን በትላንትናው ዕለት ይፋ እንዳደረገችው በሮሙ የጌሜሊ ሆስፒታል የሚገኙ ሃኪሞች ከርእሰ ሊቃነ ጳጳሱ አባ ፍራንሲንስ ሳንባ ከፍተኛ መጠን ያለው ፈሳሽ አውጥተዋል።
የሕክምና አገልግሎቱ በተደረገላቸው ወቅት አባ ፍራንሲስ እንደነበሩ እና ቆይቶም ሰውነት ውስጥ ዘልቆ ሳይገባ መደረግ የሚችል አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ እንደተደረገላቸው ታውቋል።
አባ ፍራንሲስ ካለፈው የካቲት 7 ጀምሮ፣ ሁለቱንም ሳንባቸውን ላጠቃ የሳንባ ምች እና የተወሳሰበ የመተንፈሻ አካላት ሕመም ሕክምና ሲደረግላቸው ቆይተዋል።
እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር መጋቢት 2013 ጀምሮ የጵጵስና ሥልጣናቸውን የተረከቡት አባ ፍራንሲስ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፣ ለረዥም ጊዜ ከአደባባይ ለመራቅ የተገደዱበት የአኹኑ የመጀመሪያው ነው።
አባ ፍራንሲስ ሌሊቱን ሙሉ በጥሩ ሁኔታ ተኝተው ማደራቸውን ቫቲካን ይፋ አድርጋለች። ማምሻው ላይም የተሟላ የጤና ሁኔታቸውን የሚያሳይ የሕክምና መረጃ ይፋ እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲንስ ገና ወጣት ሳሉ የሳምባቸው ክፍል ተቆርጦ እንዲወጣ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ለመተንፈሻ አካላት ሕመም ሲጋለጡ ቆይተዋል።
መድረክ / ፎረም