ኢትዮጵያ ፍላጎቶቿን ለማሟላት ወደ ጦርነት እንደማትገባ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ዛሬ ኀሙስ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የባሕር በር እና ወደብ አልባ የኾነችው ኢትዮጵያን የባለቤትነት እና የተጠቃሚነት መብት ሰሞኑን ማንሣታቸው፣ የቀጣናው አሳሳቢ ጉዳይ ኾኖ እንደሰነበተ፣ ኤኤፍፒ በዘገባው አመልክቷል።
ዛሬ ኀሙስ፣ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በዐዲስ አበባ መስቀል አደባባይ “የመከላከያ ቀን”ን ለማክበር ለተሰባሰቡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የሠራዊቱ አባላት እና የከተማዋ ነዋሪዎች፣ “ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ፣ ኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ውይይት ያስፈልገናል፤ የሚል ጥያቄ ስታነሣ፣ “ወረራ ሊካሔድ ይችላል የሚል ስጋት እንደሚደመጥ” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይኹንና፣ ኢትዮጵያ ቃታ በመሳብ በኀይል እና በወረራ ማሳካት የምትሻው አንዳችም ነገር እንደሌላት ያረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ "ይልቁንም በንግግር እና በድርድር የጋራ ጥቅሞችንና ፍላጎቶችን ለማሟላት ቁርጠኛ ነን፤” ሲሉ፣ በአጽንዖት ገልጸዋል፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በቴሌቭዥን በተላለፈ አንድ ስብሰባ ላይ፣ ቀይ ባሕር እና ዓባይ ኢትዮጵያን እንደሚበይኑ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ አገሪቱ ወደብ እንደሚያስፈልጋት ሲናገሩ ተደምጠዋል። “በሰላም አብረን መኖር የምንሻ ከኾነ፣ አንዳችን ከሌላችን የምንጋራበትን መንገድ መፈለግ አለብን፤” ብለዋል። በተለይም ከኤርትራ ጋራ ከሚታየው ውጥረት አንጻር፣ ይኸው ንግግራቸው በታዛቢዎች ዘንድ አሳሳቢ ኾኗል።
ከሠላሳ ዓመታት ጦርነት በኋላ፣ ኤርትራ በ1985 ነፃነቷን ስታውጅ፣ አሁን 120 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት የምትገመተው ኢትዮጵያ፣ የባሕር በሯንና የወደብ ባለቤትነቷን አጥታለች፡፡ እስከ 1990 ዓ.ም. ድረስ የኤርትራን ወደቦች መጠቀም ብትቀጥልም፣ በዚያው ዓመት በሁለቱ ሀገራት መካከል በተነሣው ጦርነት ምክንያት፣ ለወደብ ተጠቃሚነት ፊቷን ወደ ጂቡቲ ለማዞር ተገዳለች።
“ኢትዮጵያ ተሸንፋ አታውቅም፤ ወደፊትም አትሸነፍም፤” ሲሉ፣ የአገሪቱ ሠራዊት ሌሎችን ለማጥቃት እና ለመውረር እንደማያስብ የጠቀሱት ዐቢይ፣ “አገሪቱን ግን ይከላከላል፤” ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል።
መድረክ / ፎረም