ግርማዊነታችሁ፤ ልዑላን፤ የተከበራችሁ የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ አባላት፤ ወገኖቼ ኢትዮጵያዊያን፤ ወገኖቼ አፍሪካዊያን፤ የዓለም ዜጎች፤ ክቡራትና ክቡራን፤
እዚህ እመሃላችሁ በመገኘቴ ክብር ይሰማኛል፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ እንዲያበቃ ላበረከትኩት አስተዋፅዖ ሰለሰጠው ዕውቅናና ማበረታታት የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴን እጅግ አብዝቼ አመሰግናለሁ። ይህንን ሽልማት የምቀበለው በኢትዮጵያዊያንና በኤርትራዊያን፣ በተለይ ደግሞ ስለ ሰላም ሲሉ የመጨረሻውን መስዋትነት በከፈሉት ስም ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታም ይህንን ሽልማት የምቀበለው ይህ በሁለታችን ሀገሮች መካከል መፍትኄ ሳይገኝለት ለሃያ ዓመታት የዘለቀ ውዝግብ እንዲያበቃ በጎ ፈቃዳቸው፣ እምነታቸው፣ ቁርጠኛነታቸው ቁልፍ በነበረው በአጋሬና በሰላም ጓዴ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ስም ነው።
በተጨማሪም ይህንን ሽልማት የምቀበለው ብዙ ጊዜ የሰላም ህልማቸው ወደ ጦርነት ሰቀቀን በሚለወጥባቸው አፍሪካዊያንና የዓለም ዜጎችም ስም ነው።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነቱ ሲጫር እኔ ወጣት ወታደር ነበርኩ። የጦርነትን አስቀያሚነት በጦር ሜዳ የግንባር መስመር ላይ ሆኜ እራሴ አይቻለሁ። ጦርነትን አይተው የማያውቁ፤ ነገር ግን አካብረውና ከፍቅር ጋር የሚናገሩለት አሉ።
ፍርሃቱን አላዩትም።
ድካሙን አላዩትም።
ውድመቱን ወይም የሚደርሰውን የልብ ስብራት አላዩም። ጦርነት ከጥፋቱ ሁሉ በኋላም የሚጥለው በበረታ ኀዘን የታጨቀ ባዶነትም ተሰምቷቸው አያውቅም።
ጦርነት በውስጡ ላለ ሁሉ የገሃነም ቀጥተኛ አምሳያ ነው፤ ተመላልሼበታለሁና አውቀዋለሁ።
በጦር አውድማ ላይ ወንድማማች ሲተራረዱ አይቻለሁ። አረጋዊያን፣ ሴቶች፣ ህፃናት በሚወርድባቸው የአጥፊ ጥይትና የመድፍ ዝናብ ሥር ሆነው በፍርሃት ሲርዱ አይቻለሁ።
አያችሁ፤ እኔ የጦር ተዋጊ ብቻ አልነበርኩም። እጅግ የበዛው ክፋቱና በሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥፋት ሁሉ እማኝም ነኝ።
ጦርነት የክፉ ሰዎች ነው። የርህራኄ አልባና ሥልጣኔ የሌላቸው አረመኔዎች ነው። ከሃያ ዓመታት በፊት የድንበር ከተማይቱ ባድመ ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር የራዲዮ አገናኝ ነበርኩኝ።
ከተማይቱ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረው ጦርነት የተጫረባት ቦታ ነች።
ከነበርኩባት የቀበሮ ጉድጓድ የተሻለ የአንቴና የግንኙነት ሞገድ ለማግኘት ለአጭር ጊዜ ወደ ውጭ ወጣሁ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ስመለስ ጓዶቼ በሙሉ በከባድ መሳሪያ ድብደባ ተደምስሰው ስደርስ እጅግ የበረታ ድንጋጤ ነበር የተሰማኝ። በዚያች የተረገመች ቀን ያለቁ ወጣት የጦር ሜዳ ጓዶቼን ሁልጊዜ አስባቸዋለሁ። ስለቤተሰቦቻቸው አስባለሁ።
በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት ውስጥ ቁጥራቸው ወደ አንድ መቶ ሺህ የሚጠጋ ወታደሮችና ሲቪሎች አልቀዋል። የጦርነቱ መዘዝ ቁጥራቸው ሊነገር የማይችል ቤተሰቦችን በታትኗል። በሁለቱም በኩል የነበሩ ማኅበረሰቦችን እስከወዲያኛው አጥፍቷል።በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ የደረሰው እጅግ የሰፋ ውድመት ከጦርነቱ ባኋላ የነበረውን የምጣኔ ኃብት ሽክም አክብዶታል።
በማኅበራዊ ደረጃም ጦርነቱ እጅግ የበዛ ቁጥር ያለው ሰው አፈናቅሏል። ኑሯችንን አጥፍቷል። ሰዎች ተገድደው ከሀገር እንዲወጡ፣ ዜግነታቸውን እንዲያጡ አድርጓል።
በቀጥታ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በግንቦት 1992 ዓ.ም. ቢያበቃም ኢትዮጵያና ኤርትራ ግን ጦርነትም ሰላምም በሌሉበት አጣብቂኝ ውስጥ ለሃያ ዓመታት ያህል ተቸንክረው ኖረዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ድንበሮችን ተሻግረው ያሉ የቤተሰቦች አባላት መተያየት፣ መነጋገር ሳይችሉ ተለያይተው ቆይተዋል።በድንበሩ ሁለቱም መስመሮች በአሥሮች ሺኾች የሚቆጠሩ ወታደሮች ተፋጥጠው ቆይተዋል። መላ ሃገሪቱና መላ አካባቢው እንደነበሩት ሁሉ እነዚያ ወታደሮች ዘወትር በግጭት ጫፍ ላይ ነበሩ።
ማንኛዪቱም የድንበር ላይ አነስተኛ ግጭት ወደ ሙሉ ጦርነት ልትመልሰን ትችላለች የሚል ሥጋት ሁሉም ዘንድ ነበር።
ጦርነቱና ከዚያም በኋላ የተከተለው መፋጣጥ ለአካባቢያዊ ሰላም ሥጋት ነበር። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ቢያገረሽ መላውን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሊያናጋ ይችላል የሚል ፍርሃት ነበር፤ እውነትም ነው።
እናም ከ18 ወራት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ስሆን ያንን አቅልየለሽ ሁኔታ እንዲያበቃ ማድረግ አስፈላጊ እንደነበር በውስጤ ተሰማኝ። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ሊወርድ እንደሚችል አምን ነበር።
ሁለቱን ሀገሮች እንዲህ ለተራዘመ ጊዜ ከፋፍሎና ለያይቶ የቆየው ሃሣባዊ ግድግዳ እንደሚናድ አመንኩኝ። በቦታውም እስከወዲያኛው ፀንቶ የሚቆም የወዳጅነት፣ የመተባበርና የቅን መንፈስ ድልድይ ፈጥኖ መገንባት ነበረበት። ከአጋሬ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የሰላም ድልድይ የመዘርጋትን ሥራ የጀመርኩትም እንዲህ ነበር።
ሰላም ይፈካና ያንፀባረቅም ዘንድ ሁለታችንም ዝግጁ ነበርን። ለህዝቦቻችን ዕድገትና ብልግፅና ስንልም “ሳንጃዎቻችንን ወደ ማረሻ፤ ጦሮቻችንንም ፍሬ ወደ ወደ መልቀሚያ ሜንጦ” ለመቀየር ተስማማን።
ሃገሮቻችን ጠላትማማች አለመሆናቸውን ተረድተናል። ይልቅ ሁለታችንም የጋራ ጠላታችን የሆነው የድህነት ሰለባ ነን። እኛ ባረጁ መቃቃሮች ውስጥ ተሸንቅረን ዓለም ግን በፈጣን ሁኔታ እየተራመደና ጥሎን እየሄደ እንደሆነ ተገነዘብን። ለህዝቦቻችን እና ለአካባቢው ብልፅግና ተባብረን መሥራት እንዳለብን ተስማማን።
ዛሬ የሰላም ፍሬያችንን እየሰበሰብን ነን። ከሃያ ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ የተለያዩ ቤተሰቦች አሁን ተገናኝተዋል። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቻችን ሙሉ በሙሉ ታድሰዋል። የበረራና የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎቶች ተመልሰው ተጀምረዋል። አሁን ትኩረታችንን ለግዙፉ የምጣኔኃብት ፍላጎታችን ቁልፍ ጉልበት የሚሆኑንን የጋራ የመሠረተ-ልማት አውታሮችን ወደ መዘርጋት አዙረናል።
ሁለታችንም ሃገሮች ለሰላም ያለን ቁርጠኛነት እንደብረት እየጠነከረ ነው።
“ከሀያ ዓመታች በላይ የዘለቀ ግጭት እንደምን እንዲህ ወዳጃዊ መፍትኄ ሊያገኝ ይችላል?” ብሎ የሚደነቅ ሊኖር ይችላል።
ለሰላም የወሰድኳቸውን ዕርምጃዎች ስለመሩኝ ዕምነቶቼ ጥቂት እንዳጫውታችሁ ፍቀዱልኝ።
ሰላም ከልብ የሚመነጭ የፍቅር ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ። ሰላም የፍቅር የምጥ ልጅ ነው። ሰላምን ጠብቆ ማቆየት ደግም ከባድ ሥራ ነው። ልናከብረውና ልናበለፅገው ይገባል።
ጦርነትን ለመጀመር የሚበቃን ጥቂት ነው። ሰላምን ለመገንባት ግን መንደርና ድፍን ሃገርን ያጠይቃል።
ለእኔ ሰላምን ማበልፀግ ዛፎችን ተክሎ እንደማብቀልና እንደማሳደግ ነው።
ዛፎች ለማደግ ውኃና መልካም መሬት እንደሚያስፈልጋቸው ሁሉ ሰላምም የማይናወጥ ቁርጠኛነትን፣ የማይነጥፍ ትዕግስትን፣ ፍሬውን ለመንከባከብና ለመልቀም የሚያበቃም በጎ ፍቃድን ይጠይቃል።
ሰላም ብልፅግናን፣ ፀጥታና ደኅንነትን፣ ዕድሎችንም እንዲያፈራ መተማመንን ይጠይቃል።
ተክሎች ህይወትና ንፁህ አየር ለእኛ እንዲሰጡ እነርሱ የተቃጠለውን ጋዝ እንደሚስቡ ሁሉ ሰላምም በግንኙነቶቻችን ላይ ዳመና ሊያጠሉ የሚችሉ መጠራጠርንና ያለመተማመንን የመሳብና የመሸከም አቅም አለው። በምላሹም ለመጭው ጊዜ ተስፋን በራሳችን መተማመንንና በሰብዕና ማመንን ያጎናፅፈናል።
ይህ እየተናገርኩለት ያለሁት ሰብዕና በሁላችንም ውስጥ አለ። የኩራትና የመታበይን ጭንብል ከራሳችን ላይ ለማስወገድ ከመረጥን ልናበለፅገውና ለሌሎችም ልናደርሰው እንችላለን። ለሰብዕና ያለን ፍቅር ከራስ ወዳድነት ገዝፎ ሲወጣ ያኔ ዓለም ሰላም ምን እንደሆነ ያውቃል።
ሰላም በራዕይ መፅናትን ይጠይቃል። የእኔ የሰላም ራዕይ ደግሞ መደመር ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ ነው። ‘መደመር’ ማለት የጉልበት ሁለንተናዊ መጠናከር፣ መሰባሰብ፣ አብሮ መሥራትና የጋራ ዕጣ ፈንታ ማለት ነው። ‘መደመር’ በፖለቲካችን፣ በማኅበራዊና በምጣኔኃብታዊ ህይወታችን እየተንፀባረቀ ያለ ሃገርበቀል ሃሣብ ነው። ለእኔ ‘መደመር’ ለጋራ ህልውናችንና ብልፅግናችን ሃብቶቻችንና አቅማችንን አሰባስበን ለኢትዮጵያዊያን ፍትሃዊ፣ የመተካከል፣ ዴሞክራሲያዊና በሰብዕና የተሞላ ኅብረተሰብ ለመገንባት የሚያስችለን ዕምቅ ማኅበራዊ አቅም ነው።
በተግባር ስናየው ‘መደመር’ በመቻቻል፣ በመግባባትና በሥልጣኔ የሚያብብ አዲስ ኅብረተሰብና አዲስ ሃገራዊ ባህል ለመገንባት ካሳለፍነው ሁሉ የተሻለውን ወይም ምርጥ ምርጡን መውሰድ ነው። በአስኳሉ፤ ‘መደመር’ በጋራ ሰብዕናችን ውስጥ አንድነትን የሚሻ ሰላም ቃል ኪዳን ነው። የፍቅርን፣ የይቅርታን፣ የዕርቅንና፣ የአሰባሳቢነትን ወይም የአቃፊነትን እሴቶች ተግባር ላይ እየዋለ ሰላምን ያጠናክራል።
እኔ ምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ውስጥ ከምትገኝ በሻሻ ከምትባል ትንሽ ከተማ የወጣሁ ሰው ነኝ። የመደመር ዘር ማቆጥቆጥ የጀመረውም እዚህቹ በሻሻ ውስጥ ነው። እኔን እና እህት ወንድሞቼን ወላጆቻችን ያሳደጉን በሰብዕና ላይ የማይሰበር ማመንን እየዘሩብን ነው፡፡
መደመር “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ” “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” ከሚል አባባል ጋር ይመሳሰላል። በእኔ ትንሽ ከተማ የቧንቧ ውኃ አልነበረንም፤ መብራትና የተደላደሉ መንገዶችም አልነበሩንም። ነገር ግን ህይወታችንን በብርሃን የሞላ ፍቅር ነበረን። በእጅጉ እንተሳሰብና እንደጋገፍ ነበር። ፍቅር፣ ትኅትና፣ ብርቱ ሰብዕና፣ ትዕግስት፣ ምሥጋና፣ ፅናትና ብርታት፣ መተባበር እንደ ኃያል ጅረት ይፈስሱብን ነበር። ፍቅር፣ ይቅርታና ዕርቅ በሚባሉ ሦስት የገጠር የእግር መንገዶችም እንመላለስ ነበር። በመደመር ሃሣብ “እኛና እነርሱ” የሚባል የለም። በጋራ ፍቅር፣ ይቅርታና ዕርቅ የተጋመድን ነንና ያለው “እኛ” ብቻ ነው። የሰው ልጅ መገኛ እና የአሥራ ሦስት ወር ፀሃይ ሃገር ሰዎች ስለሆንን መደመር እንደሁ ሌላው ተፈጥሯችን ነው።
ኢትዮጵያዊያን በዕምነትና በአምልኮ ሁልጊዜም አብረን ነንና የሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች ተከታዮች በሰላም አብረን እየኖርን ነን። እኛ ኢትዮጵያዊያን ሃገራችንን ለመጠበቅ አብረን ቆመናልና ለሺኾች ዓመታት በነፃነት ኖረናል። የኢትዮጵያችን ውበት የሚያስደንቅ ብዝኅነታችን ነው። የመደመር አቃፊነት ከዚህ ታላቅ ቤተሰባችን ተነጥሎ ውጭ የሚቀር ማንም አለመኖሩ ነው። “ብቻውን የተነጠለ” ወይም “ደሴት የሆነ ማንም የለም” ም እንላለን።
በተመሣሣይ ሁኔታም የሚነጠል ማንም ሃገር የለም። ከመደመር ሃሣብ የሚነሣው የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ በዘርፈብዙ ትብብርና መልካም ጉርብትና ላይ የተመሠረተ ሰላምን ያራምዳል። “በሰላም እንድታድር ጎረቤትህ ሰላም ይደር” የሚል የቆየ አባባል አለን። በብዙ የአፍሪካ ቋንቋዎች የተነገረ አባባል ነው። የዚህ አባባል ውስጣዊ ቁምነገር መመሪያ የአካባቢያችንን ግንኙነቶች ያጠናክራል። ከጎረቤቶቻችን ጋር በሰላምና በስምምነት ለመኖር እየጣርን ነን።
የአፍሪካ ቀንድ ዛሬ ሥልታዊ ትርጉም ያለው አካባቢ ነው። የዓለም ኃያላን በአካባቢያችን የጦር ይዞታዎቻቸውን እያሰፉ ናቸው። ሽብርተኞችና ፅንፈኞችም እንዲሁ እግሮቻቸውን ለመትከል ይፈልጋሉ።
የአፍሪካ ቀንድ የኃያላን ትንቅንቅ ሜዳ ወይም ወይም የሽብር ሸቃጮች፣ የተስፋ መቁረጥና የጉስቁልና ደላሎች መሸሸጊያም እንዲሆን አንፈልግም።
እኛ የምንፈልገው የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የዕድገት ቋት እንዲሆን ነው። እኛ የምንፈልገው የአፍሪካ ቀንድ ለቀሪዋም አፍሪካ የሚበቃ የመትረፍረፍ አካባቢ እንዲሆን ነው።
እንደ ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ሰላም ላይ አቅማችንን ሁሉ ማፍሰስ አለብን። ባለፉት ጥቂት ወራት ኢትዮጵያ ለሰላም ብዙ ጥራለች፤ ብዙ አውላለች። ውጤቱን በመጭ ዓመታት እናገኛለን።
የፖለቲካ እሥረኞችን ሁሉ ለቅቀናል፤ የማጎሪያ የመበቀያ እጅግ የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎች ይካሄዱባቸው የነበሩ ተቋማትን ዘግተናል። ዛሬ ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነቷ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሞገሰች ያለች ሀገር ነች። የጋዜጠኞች አሳሪ ሃገርነቷ አክትሟል። የሁሉም የፖለቲካ ዘርፎች መሪዎች ለመንቀሳቀስና የፖለቲካ ሥራዎቻቸውን በሰላም ለማካሄድ ነፃ ናቸው። ሃሳብን በነፃነት ለመያዝና ለመግለፅ በምትሰጠው ማረጋገጫ መሰልና አቻ የሌላት ኢትዮጵያን እየፈጠርን ነን። ለሃቀኛ የብዝኃ-ፓርቲ ዴሞክራሲ መሠረት አኑረናል፤ በቅርቡም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እናደርጋለን።
እኔ ‘ሰላም የህይወት መንገድ ነው’ ብዬ በፅኑ አምናለሁ። ጦርነት የሞትና የውድመት መገለጫ ነው። ሰላም ሰባሪዎች የህይወትን መንገድ እንዲመርጡ ሰላም ሠሪዎች ማስተማር አለባቸው። በውጤቱም ዓለም የሰላምን ባህል እንዲገነባ ማገዝ አለብን። ይሁን እንጂ ሰላም በዓለማችን እንዲሰፍን በቅድሚያ ልቦናችንና አዕምሯችን ሰላማዊ መሆን አለባቸው።
ቤተሰባችን ውስጥ ሰላም መሆን አለበት፤ ሠፈራችን፣ ቀበሌያችን፣ ትናንሽና ትልልቅ ከተሞቻችን ሰላማዊ መሆን አለባቸው። በሀገሮች ውስጥና በመካከላቸው ሰላም መውረድ አለበት።
ሰላምን ጠብቆ ማቆየት ዋጋ ያስከፍላል።
‘ፍትህ በሌለበት ሰላም የለም’ የሚለው ታዋቂ መፈክር የሚያስታውሰን ሰላም የሚለመልመውና ፍሬ የሚያፈራው በፍትህ አፈር ላይ የተተከለ እንደሆነ መሆኑን ነው። በዓለም ዙሪያ ካሉት ፀብና ግጭቶች ለበዙቱ ምንጫቸው ሰብዓዊ መብቶችን አለማክበር ነው። በእኛ አህጉር አፍሪካም እውነቱ ይሄው ነው።
ከአፍሪካ ህዝብ ወደ ሰባ ከመቶ የሚሆነው ዕድሜው ከሰላሣ ዓመት በታች እንደሆነ ይገመታል። ወጣቶች ማኅበራዊና የምጣኔ ሃብት ፍትህ እንዲሰፍን እየጮሁ ናቸው። የዕድሎች እኩልነት እንዲኖርና የተደራጀ ሙስና እንዲያበቃ እየጠየቁ ናቸው።
ወጣቶች በተጠያቂነትና በግልፅነት ላይ የተመሠረተ መልካም አስተዳደር እንዲኖር አብርትተው ይጎተጎታሉ። ወጣቶቻችንን ፍትህ ከነፈግናቸው እነርሱ ሰላምን ይገፏታል።
ፍትህን ለሁሉም በእኩል የምታጎናፅፍ፣ መብቶች እኩል የሰፈኑባት፣ ለሁሉም ዜጎቿ እኩል ዕድሎች ያሉባት ኢትዮጵያን ለመገንባት እጅ ለእጅ እንድንያያዝ ዛሬ በዚህ የዓለም አደባባይ ላይ ቆሜ ለወገኖቼ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በተጨማሪም በፖለቲካና በአግሏዊነት ምክንያት የሚቀጣጠልን የፅንፈኛነትና የመከፋፈል መንገድ እንድናስወግድም በተለይ አሳስባለሁ። ታሪካችን በአቃፊ የፖለቲካ ሚዛን ላይ የተንጠላጠለ ነው። የጥላቻና የመከፋፈል ሰባኪዎች ማኅበራዊውን መገናኛ ብዙኃን እየተጠቀሙ በማኅበረሰባችን ውስጥ ትርምስ እየነዙ ናቸው። በአየር ሞገዶች ላይም የበቀልና የቁጣ ወንጌላቸውን እየሰበኩ ናቸው።
በመደመር መርኆች በመግባባት ላይ የተመሠረተ የዴሞክራሲ፣ የአቃፊነት፣ የሥልጣኔ፣ የመቻቻል ሃገራዊ ባሕል ፈጥረን አብረንም የጥላቻን መርዝ ማምከን አለብን።
ሰላምን የማነፅ ጥበብ ልቦናን፣ አሰተሳሰብን፣ ዕምነቶችንና ልማዶችን የመለወጥ የማያቋርጥ የተጠናከረ ሂደት ነው። የማፈቅራት ኢትዮጵያ ገበሬ ሥራ ዓይነት ነው። በእያንዳንዱ ወቅት መሬቱን ያዘጋጃል፣ ይዞራል፣ ያርማል፣ ተባይና አጥፊዎችን ይከላከላል። የአየሩ ሁኔታ ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎህ ሲቀድ አንስቶ ጀምበር እስክትጠልቅ ማሳው ላይ ነው። ወቅቱ ይለዋወጣል፤ የእርሱ ሥራ ግን አያልቅም፤ አይቆምም። ማሳው የሚሰጠውን ሰብል ይሰባሰባል።
የሰላምን ሰብል ለመሰብሰብ የፍቅርን፣ የይቅርታን፣ የዕርቅን ዘር በዜጎቻችን ልቦናና አዕምሮ ውስጥ መዝራት ይገባናል። የክፋትን፣ የጥላቻንና ያለመግባባትን አረም መንቀል፤ በጎም ቀን ይሁን ክፉ በእያንዳንዱ ዕለት መጣር አለብን።
እኔ “ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሄር ልጆች ተብለው ይጠራሉና” የሚለው የቅዱስ መፅሃፍ ቃል የሚመራኝ ሰው ነኝ። እንዲሁም ደግሞ “ሰዎች ሁሉ ወንድማማች ናቸው፤ በሁለት ወንድሞቻችሁም መካከል አስታርቁ” በሚለው የቅዱስ ቁርዓን ቃልም እመራለሁ።
እኔ በእያንዳንዱ ቀንና በሁሉም ወቅቶች ለሰላም በፅናት እተጋለሁ። የወንድሜ፣ የእህቴም ጠባቂ ነኝ።
ከማረፌ በፊት ማሳካት ያለብኝ የቃል ዕዳ አለብኝ። በሰላም መንገድ ላይ ረዥም ጉዞ ይጠብቀኛል።
በመጨረሻም በመደመር ላይ የቆመ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግናን በአፍሪካ ቀንድ ላይ እናፀና ዘንድ እኔና ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ በያዝነው ጥረት ከጎናችን እንዲቆም ለዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ጥሪዬን አሰማለሁ።
ሰላም ለሁላችንም፤ ሰላም ለአርበኞች እንዲሁም ለሰላም ወዳጆች።
አመሰግናለሁ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ