በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፐሎሲ ከታይዋን እንደራሴዎች ጋር ተወያዩ


የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ ከታይዋን የፖለቲካ መሪዎች ጋር ዛሬ፤ ረቡዕ ዋና ከተማዪቱ ታይፔይ ላይ ተገናኝተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ ከታይዋን የፖለቲካ መሪዎች ጋር ዛሬ፤ ረቡዕ ዋና ከተማዪቱ ታይፔይ ላይ ተገናኝተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ ናንሲ ፐሎሲ ከታይዋን የፖለቲካ መሪዎች ጋር ዛሬ፤ ረቡዕ ዋና ከተማዪቱ ታይፔይ ላይ ተገናኝተዋል።

በአፈጉባዔዋ ጉብኝት በእጅጉ የተበሳጨችው ቻይና ቁጣዋን ለማሳየት የግዛቴ አካል ነች በምትላት ታይዋን አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችና ልምምዶችን አድርጋለች።

ትናንት፤ ማክሰኞ ማታ ታዋይን የገቡት ፐሎሲ ፕሬዚዳንት ሳይ ኢንግ ዌንን አግኘተው ያነጋገሩ ሲሆን አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ ራስገዟን ደሴት ሲጎበኝ ፔለሲ የመጀመሪያ ናቸው።

“ቻይና የታዋይንን ተሳትፎ እንደምታቅበውና በተወሰኑ ስብሰባዎች ላይ እንዳትካፈል እንደምትዘጋው ሁሉ ሰዎች ወደ ታይዋን እንዳይመጡ መከልከል እንደማይችሉ እንደሚገነዘቡ ተስፋ አደርጋለሁ።” ያሉት ፐሎሲ “ይህ የወዳጅነት፣ የድጋፍ ማሳያ እንዲሁም ደግሞ እንዴት አድርገን በትብብር አብረን የተሻለ ሥራ መሥራት እንደምንችል የምንማርበት መንገድ ነው” ብለዋል።

“አሁን አፈጉባዔ ስለሆነች መምጣት የለባትም ... ምናምን ብለው በጣም ተንጫጩ፤ ከዚህ በፊት ወንዶች ሲመጡ ግን ምንም ነገር አላሉም ነበር” ሲሉ በጉብኝታቸው ዙሪያ ስለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት አካባቢ እንዲሁ እንደእርሳቸው የተወካዮች ምክር ቤቱ አፈጉባዔ የነበሩት ሪፐብሊካኑ ኒውት ጊንግሪችም ታይዋን ገብተው ነበር። ከጊንግሪች ወዲህ ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንትነት ተራ በሦስተኛ ቁጥር ላይ የሆነ በእርሳቸው ደረጃ ያለ ሌላ የአሜሪካ ባለሥልጣን ታይፔይን ረግጦ አያውቅም። ይኸው፤ ፔለሲ የመጀመሪያ ሆኑ። እንግዲህ ምነው “የጊንግሪች ጊዜ እንዲህ አልተንጫጩ?” ማለታቸው ይመስላል ... የፆታ እኩልነት ነገርንም ያስተውሏል።

በጉብኝቱ ወቅት ፕሬዚዳንት ሳይ ፐሎሲ ለደሴቲቱ ግዛት ላደረጉት አስተዋጽዖ ሜዳይ ሸልመዋቸዋል።

አፈጉባዔዋ ቆየት ብሎ በፓርላማው ፊት ባሰሙት ንግግር የታይዋን “ጥሩ ወዳጅ” ተብለው በመጠራታቸው ትልቅ ክብር የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም እርሳቸውና አብረዋቸው ያሉት የኮንግረስ ልዑካን ታይዋን የመጡት የተለየ ዓላማ ይዘው መሆኑን ገልፀዋል።

“እንደ ምክር ቤት ልዑካን በምናደርገው ጉብኝታችን ሦስት ዓላማዎች አሉን። አንደኛው፤ ደኅንነት ነው። ደኅንነት ለሰዎቻችን፤ ደኅንነት ለዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ። ሁለተኛው ብልፅግናን እስከተቻለ ድረስ ለማስፋፋት የሚያግዝ የምጣኔኃብት ጉዳይ ሲሆን ሦስተኛው መልካም አስተዳደር ነው” ብለዋል ፐሎሲ።

ቻይና የፐሎሲን ጉብኝት የተመለከተችው በተለየ መንገድ ነው። ማክሰኞ ምሽቱን በደሴቲቱ ዙሪያ ተከታታይና የተቀናጀ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን አካሂዳለች።

ቻይና ይህን ያደረገችው ዩናይትድ ስቴትስ በቅርቡ በታይዋን ጥያቄ የወሰደችው ‘እየጨመረ መጥቷል’ ያለችውና አሉታዊ ስትል የጠራችውን ድርጊት ለመበቀል መሆኑ ተመልክቷል።

“የታይዋን ነፃነት” በሚል መገንጠል ለሚፈልጉ የተገንጣዮች እንቅስቃሴን አስመልክቶም ቻይና ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።

የባይደን አስተዳደርና ፐሎሲ “የአንድ ቻይና ፖሊሲ” ተብሎ ለሚጠራው የቤጂንግ ፖሊሲ መከበር ዩናይትድ ስቴትስ በቁርጠኛነቷ እንደምትቀጥል ቢገልፁም ከታይፔይ ጋር ግን መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶችና የመከላከያ ትስስር እንዲኖር ይፈቅዳሉ።

የዋይትሃውስ ቤተመንግሥት የብሄራዊ ደኅንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ “የታይዋንን ነፃነት አንደግፍም ብለናል፤ የባህር ወሽመጥ የሚሻገሩ ልዩነቶች መፈታት ያለባቸው በሰላማዊ መንገድ እንደሆነ ይሰማናል” ብለዋል።

ቃል አቀባዩ አያይዘውም “ይህንን ጉዳይ ፕሬዚዳንት ባይደንና ፕሬዚዳንት ቺ ባለፈው ሣምንት በስልክ ያደረጉትን ውይይት ጨምሮ ከህዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተነጋገርንበታል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በዚህ በታይዋን ጉብኝታቸው ዙሪያ የተነሳው ግርግር ፐሎሲ ቀደም ሲል በጎበኟቸው የአካባቢው ሃገሮች ውስጥ ያከናወኑት ጥሩ ሥራ እንዳለ ፕሬዚዳንት ባይደን የተናገሩላቸውን ሁሉ እንዳያደበዝዘው የሰጉ አሉ።

XS
SM
MD
LG