በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ላይ ከሥልጣን ሊያስወግድ የሚችል ምርመራ እንደሚከፈት የተወካዮች ምክር ቤቱ አፈጉባዔ ናንሲ ፔለሲ በይፋ አሳወቁ።
ፔለሲ ያወጁት ይህ ምርመራ በመጭው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውስጥ የውጭ እጅ እንዲገባ ጋብዘዋልም የሚለውን ውንጀላ እንደሚያካትት ተገልጿል።
አፈጉባዔዋ የምርመራውን መከፈት ይፋ ያደረጉት በተወካዮች ምክር ቤቱ ውስጥ የምርመራውን መጀመር ከሚደግፈ የዴሞክራቲክ ፓርቲው እንደራሴዎች ጋር ሙሉ ቀን የዘለቀ ውይይት ካካሄዱ በኋላ ነው።
“ፕሬዚዳንቱ ሲፈፅሟቸው የቆዩ አድራጎቶች ሕገመንግሥቱን በብርቱ ይፃረራሉ፤ ፕሬዚዳንቱ ተጠያቂ ሊደረጉ ይገባል፤ ማንም ከሕግ በላይ አይደለም” ብለዋል ፔለሲ።
የሩሲያን ባለፈው ምርጫ ውስጥ ጣልቃ መግባትና አለመግባት ሲፈትሹ ከቆዩት ልዩ መርማሪ ሮበርት ሙለር ሪፖርት በመነሳት “ፍትሕን የማስተጓጎል ወንጀል ፈፅመዋል” በሚል በፕሬዚዳንት ትረምፕ ላይ ከሥልጣን ወደማስወገድ የሚያመራ የምርመራና የሕግ ሂደት እንዲጀመር የሚፈልጉ እንደራሴዎችን ያልተቋረጠ ጉትጎታ አፈጉባዔዋ ተቋቁመው ቆይተው ነበር።
ይሁን እንጂ ትረምፕ በቅርቡ ለዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ስልክ ደውለው በፖለቲካ ተቀናቃኛቸውና በመጭው ምርጫም ሊጋፈጧቸው በሚችሉ ባላንጣቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ልጅ ኸንተር ባይደን ላይ ምርመራ እንዲያካሂዱ የመጠየቃቸው ወሬ ከወጣ ወዲህ በፔለሲ ላይ ግፊቱ እየበረታ መምጣቱ ታውቋል።
ኸንተር ባይደን ለአንድ ዩክሬናዊ የጋዝ ኩባንያ ጠቀም ባለ ክፍያ ይሠሩ የነበረ ሲሆን ፕሬዚዳንት ትረምፕ በሙስና አድራጎት እንደሚጠረጥሯቸው ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ምርመራው በባይደን ላይ እንዲከፈት ካላደረጉ ሃገራቸው ለኪየቭ ልትሰጥ ወስና የነበረውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታግድ ትረምፕ ማስታወቃቸውና ይዘውም ማቆየታቸው ተዘግቧል።
ትረምፕ ባለፈው ሃምሌ ለዩክሬኑ አቻቸው ዜሌንስኪ ስልክ ከመደወላቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከተፈቀደው የድጋፍ ገንዘብ አራት መቶ ሚሊዮኑን እንዲይዙ ለሠራተኞቻቸው ትዕዛዝ መስጠታቸውን እራሳቸውም አረጋግጠዋል።
ይሁን እንጂ ገንዘቡን የያዙት ሌሎችም የአውሮፓ ሃገሮች የየራሳቸውን ድጋፍ እስኪሰጡ ለመጠበቅ እንጂ ከዩክሬን አንዳችም የ “እከክልኝ ልከክልህ” ምላሽ አገልግሎት ለመጠየቅ እንዳልሆነ ትረምፕ ተናግረዋል።
አፈጉባዔ ፔለሲና ሌሎችም ዴሞክራቶች የትረምፕ ጥፋቶች ከተባለው “የስልክ ጥሪም የከፉ ናቸው” ይላሉ።
የዛሬውን የናንሲ ፔለሲን የኢምፒችመንት ምርመራ መከፈት ተከትሎ ፕሬዚዳንት ትረምፕ ባወጡት ትዊት “ያደረግኩት በጣም ወዳጃዊና ተገቢ የስልክ ንግግር እንደሆነ ታዩታላችሁ። አንዳችም ጫና የለበትም። ከጆ ባይደንና ከልጁ በተለየ ሁኔታ ‘እከክልኝ ልከክልህ’ የለበትም። እጅግ የከበደና አፍራሽ የሆነው ‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’ ለማስቀጠል ካልሆነ በስተቀር አንዳች እርባና የለውም” ብለዋል።
ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ጋር ያደረጉትን የስልክ ምልልስ ሙሉ ቃል ሳይቀነስና ሳይደለዝ ሙሉውን በይፋ እንደሚያወጡ ፕሬዚዳንቱ ቃል ገብተዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ዜሌንሲ ጋር ነገ፤ ረቡዕ ኒው ዮርክ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ተገናኝተው እንደሚወያዩ ታውቋል።
ስለተፈጠረው ንግግርና ውዝግብ ቪኦኤ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪን ጠይቋቸው "እኛ ነፃ ሃገር ነን፤ ለምንም ዝግጁ ነን" ከማለት ያለፈ የተናገሩት ከፕሬዚዳንት ትረምፕ ጋር የሚኖራቸው የነገው ንግግር ሞቀ እንደሚሆን ብቻ ነው።
ለተጨማሪ ከታች የተያያዘውን ማገናኛ ይከተሉ።
https://www.voanews.com/usa/house-speaker-pelosi-opens-trump-impeachment-inquiry
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ