የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ከህወሓት ጋር የሚደራደረው ምን ዓይነት ሁኔታዎች ሲሟሉ እንደሆነ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ በሥራ ላይ መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
ድረድሩም የሚካሔደው በዚሁ ኮሚቴ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ኮሚቴው ለድርድር በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ጥናት አጠናቆ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ለሚኒስተሮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል።
መንግሥታቸው ሰላምን ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግም የተናገሩ ሲሆን፣ “የተለያዩ ችግሮች ውስጥ ይገኛል” ላሉት የትግራይ ሕዝብ በማሰብ የተወካዮች ምክር ቤትም የሰላም ጥረቶችን እንዲደግፍ ጠይቀዋል፡፡ በተለያዩ ሀገራት በድብቅ ድርድር እየተካሔደ እንደሆነ የሚሰራጩ መረጃዎችን ሐሰት ናቸው ብለዋል፡፡
“በሕግ ማስከበር ስም በአማራ ፋኖ ላይ የጅምላ እስር እና አፈና ተፈጽሟል” በሚል የሚቀርቡ ክሶችን ሐሰት እና በፋኖ ስም የመጠቀም ሙከራ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ የሚዲያ ባለሞያዎች እስርም ሕግ የማስከበር እርምጃ አካል ነው ብለዋል፡፡