በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኦፌኮና ኦነግ መንግሥት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ነው ያሉት ግድያና እስራት እንዲቆም ጠየቁ


ኦፌኮና ኦነግ መንግሥት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ነው ያሉት ግድያና እስራት እንዲቆም ጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:41 0:00

ኦፌኮና ኦነግ መንግሥት በንጹሃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ነው ያሉት ግድያና እስራት እንዲቆም ጠየቁ

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ /ኦፌኮ/ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ "መንግሥት በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ግድያና እስራት ያቁም" ሲሉ አሳስበዋል።

መንግሥት ጀምሮታል ያሉትን ጦርነት አቁሞ ከታጣቂዎች ጋር በመደራደር ለችግሩ የፖለቲካ እልባት መስጠት አለበት ሲሉም ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጠይቀዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ ፓርቲ ትናንት "የንጹኃን ዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታን መወጣት ያለመቻል የሥርዓቱ ውድቀት ማሳያ ነው!" በሚል ርዕስ ስር ባወጣው መግለጫ “ኦሮምያ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ በዚህ ሚያዝያ ወር ውስጥ 278 ንፁሃን ሰዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በሌሎችም ታጣቂዎች ተገድለዋል” ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው ነገር የለም። ሆኖም ትናንት በተቀራራቢ ጉዳይ ላይ ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩት የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ፤ “መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ያለው በሸኔ ካምፖች እና የሸኔ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ ላይ ነው።” ብለዋል።

ፓርቲያቸው ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “አብዛኛው ኦሮምያ ክልል ጦርነት እየተካሄደ ነው” ብለዋል። “ለምሳሌ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከ278 ሰዎች በላይ ተገድሏል” ብለዋል።

የሟቾችን ቁጥርን በተመለከተ በኦሮምያ እና ሌሎችም ክልሎች ውስጥ ካሉ አባሎቻቸውና ከሕዝቡ መረጃዎቹን ማግኘታቸውን ጠቅሰው ቁጥራቸው የበዛ ሰዎች መታሰራቸውን ተናግረዋል። “ዋናው ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። ለፖለቲካ ጥያቄም የሚያስፈልገው ፖለቲካዊ መልስ እንጂ በጠመንጃ መሆን የለበትም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር የለም። በእኛም በኩል በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው። ሆኖም በኦሮምያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በተፈፀመ የአየር ጥቃትን በተመለከተ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ትላንት በሰጡት ምላሽ፤ “መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ያለው በሸኔ ካምፖች እና የሸኔ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ ላይ ነው።” ብለዋል።

በሌላ በኩል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ተመሳሳይ ይዘት ያለው መግለጫ ያወጣ ሲሆን የፓርቲው ጊዜያዊ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ ከኅብረተሰቡና በየአካባቢው ከሚገኙ የፓርቲያቸው አደረጃጀት አባላት ባገኙት መረጃ መሰረት "በኢትዮጵያ ተገኘ ከተባለው ለውጥ ሦስት አራት ዓመታት ወዲህ የመንግሥት ኃይሎች በዜጎች ላይ ዘርፈ ብዙ የሆኑ እንግልትና ሞት ከማድረስ በዘለለ የኦሮሞ ሕዝብ ተቋማትና መገለጫዎችን እያዳከሙና እያፈረሱ ነው" ብለዋል።

በሌላ በኩል በሸኔ ላይ ጥቃት መክፈቱን የተናገሩት ዶ/ር ለገሰ ቱሉ “የአገር መከላከያ ሠራዊት እርምጃ እየወሰደበት ነው” ብለዋል። በአራቱ የወለጋ፣ እንዲሁም የምዕራብ ሸዋ ዞኖችና ሌሎችም አካባቢዎች ጥቃቱ በተመሳሳይ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረው “የመንግሥት ኃይሎች እህል ይዘርፋሉ፣ ነዋሪ ያዋክባሉ የሚሉና የመሳሰሉ የነዋሪዎች አቤቱታዎችን በተመለከተ “አድራጎቶቹን የሚያካሂደው የመንግሥት ኃይል ሳይሆን ሸኔ ነው” ብለዋል።

XS
SM
MD
LG