በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አይሲስ የዓለም እጅግ የበረታው ሥጋት ነው - ፕሬዚዳንት ኦባማ


ፕሬዚዳንት ኦባማ የአይሲስ ስትራተጂያቸውን አሳወቁ - ረቡዕ፣ ጳጉሜ 5/2006 ዓ.ም፣ ዋይት ሃውስ፣ ዋሺንግተን
ፕሬዚዳንት ኦባማ የአይሲስ ስትራተጂያቸውን አሳወቁ - ረቡዕ፣ ጳጉሜ 5/2006 ዓ.ም፣ ዋይት ሃውስ፣ ዋሺንግተን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢራቅና በሶሪያ እሥላማዊ መንግሥት ነኝ የሚለውን ታጣቂና ፅንፈኛ ቡድን እመታለሁ ያሉበትን ባለአራት ደረጃ ሥልት ይፋ አደረጉ፡፡

የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአይሲል ላይ የነደፉትን ስትራተጂ ያሳወቁበትን ንግግር ሲያደርጉ - ረቡዕ፤ ጳጉሜ 5/2006 ዓ.ም - ዋይት ሃውስ ዋሺንግተን ዲሲ
የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአይሲል ላይ የነደፉትን ስትራተጂ ያሳወቁበትን ንግግር ሲያደርጉ - ረቡዕ፤ ጳጉሜ 5/2006 ዓ.ም - ዋይት ሃውስ ዋሺንግተን ዲሲ

please wait

No media source currently available

0:00 0:07:21 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

ፕሬዚዳንት ኦባማ የአይሲስ ስትራተጂያቸውን አሳወቁ

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በኢራቅና በሶሪያ እሥላማዊ መንግሥት ነኝ የሚለውን ታጣቂና ፅንፈኛ ቡድን እመታለሁ ያሉበትን ባለአራት ደረጃ ሥልት ይፋ አደረጉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በቴሌቪዥን ባደረጉትና የሃገሪቱ ጣቢያዎች በቀጥታ ባስተላለፉት ንግግራቸው ኢስላሚክ ስቴት ዛሬ የዓለም እጅግ አሳሳቢው ሥጋት ነው ብለዋል፡፡

“ኢስላሚክ ስቴት (እሥላማዊ መንግሥት) ሙስሊምም አይደለም፣ መንግሥትም አይደለም፤ በንፁሃን ሰዎች ላይ ግድያ የሚያካሂድ አንድም ሃይማኖት የለም፤ ደግሞም ከአይሲል ሰለባዎች እጅግ ስፋት ባለው ሁኔታ የሚበዙት ሙስሊሞች ናቸው፤ አይሲል በውኑ መንግሥት ሳይሆን ቀደም ሲል ኢራቅ ውስጥ የአልቃይዳ ግብር አበር የነበረ ነው፡፡ የተፈጠረለትን የሃይማኖት ጎራ የለየ መናቆር እና የሶሪያን ጦርነት አጋጣሚ ተጠቅሞ ኢራቅና ሶሪያ ውስጥ መሬት መቆጣጠር ችሏል፡፡ ዕውቅና የሰጠው አንድም መንግሥት የለም ወይም አሸንፎ እየገዛቸው ያሉት ሕዝቦችም አልሰጡትም፡፡ የጠራና ቀላል የሆነው ጉዳይ አይሲል መንገዱ ላይ የሚቆምን ሁሉ የሚገድል የሽብር ቡድን ነው” ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጡት የአይሲስን ተዋጊዎች አዳክመን በሂደትም እንደመስስበታለን ያሉት ሶሪያ ውስጥ የአየር ድብደባዎችን ማካሄድንና አሁን ኢራቅ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ድብደባ ማጠናከርን የጨመረ ባለአራት ደረጃ ስትራተጂ ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮቿ በጋራ የሚከተሉት መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ኢራቅ ውስጥ የተጀመረው የአየር ዘመቻ እንደሚቀጥል የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኦባማ ለኢራቅ እና ለኩርድ ኃይሎች የሥልጠና፣ የሥለላና የትጥቅና መሣሪያ ድጋፍ የሚሰጡ ግን ቀጥተኛ ውጊያ ውስጥ የማይገቡ 475 ወታደሮችን በተጨማሪነት እንደሚልኩ ተናግረዋል፡፡

“ይሄ የእኛ የብቻችን ጦርነት አይደለም - አሉ ፕሬዚዳንት ኦባማ - የአሜሪካ ጉልበት ወሣኝ ልዩነት ሊያመጣ ይችላል፤ ነገር ግን ኢራቃዊያን ለራሳቸው ማድረግ የሚገባቸውን እኛ ልናደርግላቸው አንችልም፡፡ የአካባቢያቸውን ደኅንነት በመጠበቅ በኩልም አረብ አጋሮቻችን እኛ ልንተካ አንችልም፡፡ ለዚህ ነው የዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ኢራቃዊያን አሣታፊ መንግሥት በመመሥረታቸው ጉዳይ ላይ ይመረኮዛል ብዬ ስጎተጉት የቆየሁት፡፡ አሁን ሰሞኑን ያንን ዓይነት መንግሥት መሥርተዋል፡፡ እናም በዚህ ምሽት አዲስ የኢራቅ መንግሥት ባለበት ሁኔታ፣ በውጭ ካሉ አጋሮቻችንና በሃገር ቤትም ከተወካዮች ምክር ቤቱ ጋር መክሬ ሳበቃ አሜሪካ ይህንን የሽብር ሥጋት ለመቀልበስና ለማባረር መሠረተ-ሠፊውን ጥምረት እንደምትመራ ማወጅ እችላለሁ፡፡”

አፈጉባዔ ጆን ቤነርና ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራው ጥምረት የውጭ ተዋጊዎች ወደ “እሥላማዊ መንግሥት” እንዳይገቡ በመከላከልና በታጣቂዎቹ ምክንያት ለተፈናቀሉት ሰብዓዊ እርዳታ በመስጠት ፀረ-ሽብር ሥራውን እንደሚያጠናክርና እንደሚያሳድግ አመልክተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ አክለውም ዩናይትድ ስቴትስ ፅናት ያለውንና የማይታጠፈውን ጥረቷን የእሥላማዊ መንግሥት ፅንፈኞችን ካሉበት ሁሉ ለማጥፋት የአየር ኃይሏን እየተጠቀመችና ምድር ላይም ላሉት የአጋሮቻችን ኃይሎች ድጋፍ እየሰጠች ትመራለች” ብለዋል፡፡

ለዩናይትድ ስቴትስ ሥጋት የሚደቅኑ ሽብርተኞችን የመንና ሶሪያ ውስጥ እያሳደዱ የማጥፋት ስትራተጂ ለዓመታት የቀጠለ ሥራ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ኦባማ “አሜሪካ ወታደሮቿን በውጭ ሃገር መሬት ላይ በሚካሄድ ጦርነት ውስጥ አታስገባም፤ ይሁን እንጂ ቁልፍ ጥቅሞቿን አደጋ ላይ በሚጥል ማንም ላይ ኃይሏን ትጠቀማለች” ብለዋል፡፡

የኢስላሚክ ስቴትን ሥጋት ለመቆጣጠር መውሰድ ለሚፈልጉት እርምጃ ሥልጣንና ኃይሉ እንዳላቸው ገልፀው “ይሁን እንጂ አሜሪካዊያን አንድ መሆናችንን ለዓለም ለማሳየት የተወካዮች ምክር ቤቱን ቢደግፋቸው በፀጋ እንደሚያዩት አመልክተዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ በሽብር ፈጠራ ላይ ለሚካሄደው ትግል መሪ መሆኗን ጠቁመዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአይሲል ላይ የነደፉትን ስትራተጂ ያሳወቁበትን ንግግር ሲያደርጉ - ረቡዕ፤ ጳጉሜ 5/2006 ዓ.ም - ዋይት ሃውስ ዋሺንግተን ዲሲ
የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአይሲል ላይ የነደፉትን ስትራተጂ ያሳወቁበትን ንግግር ሲያደርጉ - ረቡዕ፤ ጳጉሜ 5/2006 ዓ.ም - ዋይት ሃውስ ዋሺንግተን ዲሲ

“በዚህ ያልተረጋጋ ዓለም በውጭ የአሜሪካ አመራር በብቸኝነት የማይቋረጥ ነው፤ ለመምራትም ያለብንን ኃላፊነት በፀጋ እንቀበለዋለን” ብለዋል፡፡

ዛሬ አሜሪካ ላይ የሽብር ጥቃት የተፈፀመበት አሥራ ሦስተኛ ዓመታ መታሰቢያ ዋዜማ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ኦባማ በአሜሪካ ምድር ላይ ከኢስላሚክ ስቴት ያጠላ ተለይቶ የሚታይ ሥጋት እንደሌለ፤ ነገር ግን በውጭ ባሉ አሜሪካዊያንና የዩናይትድ ስቴትስ አጋሮች ላይ እየተካሄደ ያለ አደጋ የደቀነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

“አሜሪካን የተተናኮለ መሸሸጊያ የለውም” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአይሲል ላይ የነደፉትን ስትራተጂ ይፋ ያደረጉበትን ንግግር ሙሉ ቃል በእንግሊዝኛ ለማዳመጥና የእንግሊዝኛውን ፅሁፍ ለማግኘት ከታች የተቀመጠውን ማገናኛ ተጭነው ይከተሉ፡፡

http://www.whitehouse.gov/blog/2014/09/10/president-obama-we-will-degrade-and-ultimately-destroy-isil

XS
SM
MD
LG