ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ፥ ባለቤታቸው ሚሼል እና ሌሎች ባለሥልጣናት የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ጄት አይሮፕላኖች ኒው ዮርክ ውስጥ ከዓለም የንግድ ማዕከል መንትያ ሰማይ ጠቀስ ፎቆች ጋር በተላተሙበት ሰዓት ማለትም ልክ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከ 46 ደቂቃ ላይ ሁለት ባሕር ወለድ ወታደሮች በዋይት ሃውስ የደቡባዊ ክንፍ በሮች ብቅ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ሁለት፤ አንደኛው የአሜሪካን ባንዲራ የያዘ አንደኛው የክብር ዋሽንት የሚነፋ ሆነው ለወደቁት ሞገስን ሰጡ፡፡
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሁለተኛው የበረራ ቁጥር 11 የሆነው የአሜሪካን አየርመንገድ አይሮፕላን የኒውዮርኩን የዓለም የንግድ ማዕከል ሰሜናዊ ሕንፃ የመታበት ጊዜ ነበር በሥፍራው የተገኘው የክብር ዘብ ሙሉ የብረት ሰላምታ ሰጥቶ ባንዲራውን ከፍ አደረገ፡፡
ባራክ ኦባማ እና ሚሸል ኦባማ ራሣቸውን ዝቅ አድርገው ለክብር ይነፋ የነበረውን ትራምፔት አስተናገዱ፡፡
ከዚህ በኋላ ሚስ እና ሚስተር ኦባማ፣ እንዲሁም ባለሥልጣናቱ 187 ሰዎች ወደተገደሉበት ሦስተኛው የሽብር ጥቃት በአሜሪካን አየርመንገድ አይሮፕላን የበረራ ቁጥር 77 ወደተፈፀመበት የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤቱ ተጉዘው ተመሳሳይ የሕሊና ፀሎት መርተዋል። “ጊዜው ይርዘም እንጂ - አሉ ፕሬዘዳንቱ ወገኖቻችን አይረሱም፡፡ እነርሡ መስዋዕትነት በመክፈላቸው ምክንያት ነው ባንድ ላይ ሆነን ሀገራችን ድረስ ሠይጣናዊ ተልዕኮውን በፈፀመው አሸባሪ ድርጅት ላይ አሽመድማጅ እርምጃ የወሰድነው። ዛሬ የአልቃይዳው አመራር ድባቅ ተመትቷል። ኦሳማ ቢን ላደን ከእንግዲህ ወዲያ ሊያሠጋን አይችልም። የሀገራችን ደህንነት ተጠብቋል፥ ሕዝባችንም ከጥቃቱ ፈጥኖ አገግሟል»
ምክትል ፕሬዘዳንቱ ጆ ባይደን ደግሞ ሦስተኛውን አውሮፕላን መንገደኞች ካሸባሪዎች ለማስለቀቅ ሲታገሉ ወድቆ በተከሰከሰበት ሻንክስቪይ ፔንሲልቬንያ በሚካሄድ ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር አሰምተዋል።
ቤተሰቦች እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ጥቃቱ በተፈጸመበት ሥፍራ በቆመው ሃውልት ላይ የተቀረጸውን የጥቃቱን ሰለባዎች ስም ያነባሉ።
የመስከረም አሥራ-አንዱ ጥቃት፣ በአሜሪካ ውስጥ አዲስ የአንድነት መንፈስ ፈጥሏል ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚስተር ሌዖን ፓኔታ ተናግረዋል።
“የመስከረም አሥራ አንዱ ድንጋጤና ኀዘን፣ አዲስ የአንድነት መንፈስ ወለደ። ይህ ዓይነቱ ጥቃት እንደማይደገምም አረጋገጠ። ጥቃቱን ተቋቁመን ሕይወታችንን በአግባቡ ለመምራት፣ ቁጭት የተመላበትን ቁርጠኛነት አነሳሳ።አሸባሪዎች ጥንካሬያችንን ለመፈታተን ያደረጉት ሙከራ፣ አሜካውያን ላገራቸው ያላቸውን ከፍተኛ መንፈስ አጠናክሯል።” ብለዋል የመከላከያ ሚኒስትሩ፡፡
ከዚህ በፊት እንደነበረው የመስከረም 11 መታሰቢያ፣ ዛሬም ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማና ባለቤታቸው ሚሼል ኦባማ፣ በኢራቅና አፍጋኒስታን ጦርነት የተሰዉ አሜካዊያን ወታደሮች ያረፉበትን የአርሊንግተኑን ብሔራዊ መካነ መቃብር ጎብኝተዋል።
ማምሻውን ፕሬዚደንቱ በዋልተር ሪድ ብሔራዊ ሆስፒታል የጤና ማዕከል ተገኝተው፣ የቆሰሉ አሜሪካውያን ወታደሮችን ይጎበኛሉ።