በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በሺሆች የሚቆጠሩ ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቁን አስታወቀ


የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በሺሆች የሚቆጠሩ ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቁን አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:15 0:00

የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ታራሚዎችን በይቅርታ መልቀቁን ከትናንት በስተያ፤ ቅዳሜ አስታውቋል።

ይቅርታው የተፈቀደው በክልሉ ህገ መንግሥት ለታራሚዎች የሚሰጥን ይቅርታ በሚመለከተው አንቀፅ መሠረት መሆኑን የክልሉ አቃቤ ህግ መሥሪያ ቤት ገልጿል።

ክልሉ ውስጥ ‘በፖለቲካ ምክንያት ተይዘዋል’ ሲሉ ተቃዋሚዎች አቤቱታ የሚያሰሙባቸውን ሰዎች በሚመለከት የተሰጠ ማብራሪያ የለም።

ይቅርታው በስርቆት፣ በዘረፋና በሙስና ወንጀሎች የተፈረደባቸውን ታራሚዎች እንደማይመለከት የኦሮምያ ምክትል አቃቤ ህግ ፍቅር ዘላለም ለቪኦኤ ገልፀዋል።

ስለ ይቅርታ አሰጣጡ አሠራር ማብራሪያ የሰጡት አቃቤ የክልሉ አቃቤ ህግ ፤ “በዚህ አዋጅ አንድ ሰው ይቅርታ የሚደረግለት ሁኔታ በግልፅ ተቀምጧል። አንደኛ፣ ተፈርዶባቸው ማረምያ ቤት ውስጥ ለሚገኙ፣ እንዲሁም የይቅርታ ማመልከቻ ሲቀርብ አቤቱታ አቅራቢው በፈፀመው ወንጀል መፀፀቱን በማረምያ ቤቱ በኩል መቅረብ አለበት። ሁለተኛ፣ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ የተፈረደባቸው ከተጎጂ ቤተሰቦች ጋር እርቅ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ያም በኮሚቴ በትክክል መቅረብ አለበት። በዚህ መሠረት ነው ይቅርታው የተሰጠው። “ ብለዋል።

በሌላ በኩል ግን አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በክልሉ ፀጥታ ኃይል ያለአግባብ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆኑን በመግለፅ ኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በየወቅቱ ይገልፃሉ። በሺሆች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው እንደታሠሩም ይናገራሉ።

በቅዳሜው የምኅረት ውሣኔና አቤቱታዎቻቸውን በሚመለከት የኦሮሞ ፈደራሊስት ኮንግረስ ከፍተኛ ፀሐፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ ዛሬ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል የክልሉ መንግሥት ‘ፈትቻለሁ’ ካላቸው ከ3600 በላይ ታራሚዎች ውስጥ የፓርቲው አባላት እንደሌሉ ገልፀዋል።

አቶ ጥሩነህ አክለውም ዛሬም ድረስ “የፓርቲያቸው አባላት በመንግሥት መዋቅር ያለአግባብ እንግልትና እሥራት እየደረሰባቸው ነው” ብለዋል።

ለዚህና ተመሳሳይ አቤቱታዎች ምላሽ የሰጡት ምክትል አቃቤ ህግ ፍቅር ዘላለም ይቅርታው የሚመለከተው በፍርድ ሂደት ውስጥ አልፈው ማረምያ ቤቶች ውስጥ ያሉትን ብቻ መሆኑን ገልፀው “’ከሕግ አካሄድ ውጭ የታሠሩ አሉ’ በሚል ለሚቀርበው አቤቱታ መንግሥት በሌላ አሠራር ይወስናል” ብለዋል።

XS
SM
MD
LG