በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የወልቃይት ነዋሪዎች ለማንነት ጥያቄአቸው ምላሽ እንዲሰጣቸውና በጀትም እንዲመደብላቸው ጠየቁ


የወልቃይት ነዋሪዎች ለማንነት ጥያቄአቸው ምላሽ እንዲሰጣቸውና በጀትም እንዲመደብላቸው ጠየቁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:31 0:00

የወልቃይት ነዋሪዎች ለማንነት ጥያቄአቸው ምላሽ እንዲሰጣቸውና በጀትም እንዲመደብላቸው ጠየቁ

የዐማራ እና የትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡበት የወልቃይት አካባቢ በሚገኙት፥ የዳንሻ፣ ማይካድራ እና ሑመራ ከተሞች፣ ለማንነታቸው ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጣቸውና በጀትም እንዲመደብላቸው የሚጠይቁ ሰልፎች ተካሔዱ፡፡ የትግራይ ክልል፣ “ጥያቄው የተነሣው በሰፋሪዎች ነው፤” ብሏል።

የዐማራ እና የትግራይ ክልሎች የሚወዛገቡበት፤ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ “ምዕራብ ትግራይ” በሚል በትግራይ ክልል አስተዳደር ሥር የቆየው እና ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በሚል በተዋቀረው አስተዳደር ሥር በሚገኙት፥ ዳንሻ፣ ማይካድራ እና ሑመራ ከተሞች፣ ትላንት እሑድ፣ ግንቦት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዷል።

ሰልፈኞቹ ከያዟቸው በርካታ መፈክሮች መካከል፣ “ዐማራ ነን አልን እንጂ ዐማራ እንኹን ብለን አልጠየቅንም” የሚል ይገኝበታል፡፡ በሰልፉ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸው ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁንና በስልክ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የሑመራ ከተማ ነዋሪ፣ ሰልፉ የተካሔደው፣ “ዐማራ ነን ለሚለው ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጣቸውና ማንነታቸው እንዲጸድቅላቸው” ለመጠየቅ እንደኾነ ተናግረዋል።

ሌላው፣ የሰልፉ አስተባባሪ እንደኾኑ በስልክ የገለጹልን አቶ ግርማይ ገብረ ሕይወት፣ ሰልፉን ያካሔዱት ባለርስቶች መኾናቸውን ገልጸዋል።

ሰልፉ፥ ከዳንሻ፣ ከማይካድራ እና ከሑመራ በተጨማሪ፣ በዓዲረመፅ፣ ባዕኸር እና ሌሎችም ከተሞች መካሔዱን አስተባባሪው ተናግረዋል። ለሦስት ዓመታት ያህል፣ ለአካባቢው የመንግሥት በጀት እንዳልተመደበለት የገለጹት አቶ ግርማ፣ ሰልፉ ለዞኑ አስተዳደር በጀት እንዲመደብለት ግፊት ለማድረግም የተካሔደ እንደኾነ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ ማክሰኞ፣ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የትግራይ ክልል ተፈናቃይ ሰልፈኞች፣ በመቐለ ከተማ በአካሔዱት ሰላማዊ ሰልፍ፥ የፕሪቶርያው ስምምነት በሙሉ ቃሉ እና በሙሉ መንፈሱ እንዲተገበር፣ ሰብአዊ ድጋፉ እንዲቀጥልና ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ፣ የሑመራ ከተማ ሰልፍ ተሳታፊዋ፥ በትግራይ ክልል የተካሔደው ሰልፍ፣ ከእነርሱ ጥያቄ ጋራ የተቃረነ እንደኾነ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ሂውማን ራይትስ ዋች፣ በምዕራብ ትግራይ፣ “ዘር ማጽዳት ተፈጽሟል” ሲል፣ ባለፈው ሳምንት በአወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡ “የዐማራ ኃይሎች እና የአካባቢው ባለሥልጣናት፣ በጉልበት የትግራይ

ተወላጆችን ማፈናቀላቸውን ቀጥለዋል፤” ሲል ዐርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ይህን ተግባር በመፈጸም ላይ የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎችን እንዲያግድ፣ እንዲመረመርና በአግባቡ እንዲቀጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ትላንት በሑመራ የተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ አቶ ግርማ፣ የመብት ድርጅቶቹ የሚያወጧቸው ሪፖርቶች፣ አልተቀበሏቸውም።

የትግራይ ክልል ኮምዩኒኬሽንስ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ከክልሉ መውጣት እንደሚገባቸው ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውሰው፤ በስምምነቱ መሠረት ጥያቄ የሚነሣባቸው ቦታዎችም፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንደሚፈታ መቀመጡን ጠቁመዋል። ትላንት የተካሔደው ሰልፍ ግን፣ ይህን የሰላም ስምምነት ሒደት የሚያደናቅፍ ነው፤ ብለዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርት ምዕራብ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ በደል በመፈፀምና በዘር ማጥፋት ወንጀል ስማቸው በሪፖርቱ ላይ ከተጠቀሱት አንዱ የኾኑትና፤ በዐማራ ክልል ቴሌቭዥን ጣቢያ ላይ በሰልፉ ላይ ያደረጉትን ንግግር በሚቀርብበት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ መኾናቸው የተነገረው ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱ አካባቢው የዐማራ መኾኑን ተናግረዋል።

ይኸው የዐማራ እና የትግራይ ክልሎች የሚወዛገቡበት የወልቃይት አካባቢ፣ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ፣ “ምዕራብ ትግራይ” በሚል፣ በትግራይ ክልል አስተዳደር ሥር የነበረ፤ ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በሚል በተዋቀረ አስተዳደር ሥር ይገኛል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት እና ህወሓት፣ በፕሪቶርያ በደረሱበት የሰላም ስምምነት መሠረት፣ የአወዛጋቢ ቦታዎች ጥያቄ በሕግ እንደሚፈታ ነው የተገለጸው፡፡

XS
SM
MD
LG