በናይጄሪያ ባለፈው ቅዳሜ የተደረገው ምርጫ ግዜያዊ ውጤት በመውጣት ላይ ቢሆንም ተቃዋሚው ፓርቲዎች ግን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል።
እስከአሁን በተደረገው ቆጠራ የገዢው ‘ኦል ፕሮግረሲቨ ኮንግረስ’ ፓርቲ ቦላ ቲኑቡ 36 በመቶ ወይም 7 ሚሊዮን ድምጽ በማግኘት እየመሩ ሲሆን፣ የተቃዋሚው ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲው አቲኩ አቡባካር 30 በመቶ ወይም 6 ሚሊዮን ድምጽ በማግኘት ይከተላሉ።
የሰራተኛ ፓርቲውን የሚወክሉት ፒተር ኦቢ 20 በመቶውን ወይም ከተቆጠረው ድምጽ ውስጥ 3.8 ሚሊዮን አግኝተዋል። ዛሬ ተጨማሪ የድምጽ ውጤቶች እነድሚወጡ ይጠበቃል።
ጊዜያዊ ውጤቶቹ ይፋ የሆኑት በሃገሪቱ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚሽን ሲሆን፣ አቡጃ ወደሚገኘው የቆጠራ ማዕከል መላክ ይኖርበታል ተብሏል።
የምርጫ አፈጻጸሙ የሚታመን አይደለም በሚል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጤቱን እንደማይቀበሉት አስታውቀዋል። ምርጫ ቦርዱ ጥቅም ላይ ያዋለው አዲስ ቴክኖሎጂ ተደጋጋሚ እክል አጋጥሞት እንደነበር ተነግሯል።
ቦርዱ የምርጫውን ውጤት ከምርጫ ጣቢያዎቹ በቀጥታ ወደ ድህረ ገጹ ለመጫን አስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ጣቢያዎች ባጋጠማቸው ቴክኒካዊ ችግር ያንን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በመሆኑም ውጤቱ በተለመደው መንገድ እንዲሰበሰብ ግድ ብሏል።
በምርጫው ሂደት የተቆጡ ሰዎች በመኖራቸው ሁከት እንዳይከተል ተሰግቷል።
በአፍሪካ ሕዝብ ተጨናንቆ ከሚኖርባችቸው ቦታዎች አንዱ በመሆኑ የሚታወቀው በ’ሌጎስ አይላንድ’ የሚገኘው ገበያ ሱቆች ዝግ ሆነው ሲውሉ መንገዶችም ጭር ብለው ተስተውለዋል።