በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዚምባብዌ ከምርጫ ጋራ በተገናኘ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚን ጠርታ አነጋገረች


ዚምባብዌ ከምርጫ ጋራ በተገናኘ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈጻሚን ጠርታ አነጋገረች
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:16 0:00

በዚምባብዌ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ በዚያች አገር ያሉ ዜጎች፣ ለምርጫ እንዲመዘገቡና በምርጫው እንዲሳተፉ በማኅበራዊ ሚዲያ ተከታታይ ማስታወቂያ ማውጣቱን ተከትሎ፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በዚምባብዌ የአሜሪካ ኤምባሲ ተጠባባቂ አምባሳደርን ጠርቶ አነጋግሯል።

የዚምባብዌ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሊቪት ሙጌጆ፣ ትላንት ማክሰኞ እንደተናገሩት፣ በአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ የኾኑትን ኢሌይን ፍሬንችን፣ መሥሪያ ቤታቸው ጠርቶ፣ ከአገሪቱ ምርጫ ጋራ በተያያዘ፣ ኤምባሲው በማኅበራዊ ሚዲያ ያወጣቸውን ማስታወቂያዎች አስመልክቶ አነጋግሯቸዋል።

ከኤምባሲው በርካታ የትዊተር መልዕክቶች መካከል፣ “ለምርጫ ተመዝገቡ፤ ድምፃችኹ መሰማቱን አረጋግጡ፤” የሚለው ማስታወቂያ እንደሚገኝበት የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ ጉዳይ አስፈጻሚዋ ኢሌይን ፍሬንች፣ የውጪ ጉዳይ ተጠባባቂ ሚኒስትር ከኾኑት ሮፊና ቺካቫ ጋራ መነጋገራቸውንና “የአሜሪካ ኤምባሲ፥ ማኅበረሰብን ማንቃት በሚመስል ሥራ ውስጥ መግባቱን፣ እንዲሁም በዚምባብዌ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ እንዳሳሰባቸው” ነግረዋቸዋል፤ ብለዋል።

የኤምባሲው ቃል አቀባይ ሜግ ሪግስ፣ የኤምባሲው ጉዳይ አስፈጻሚ እና የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣኗ ተገናኝተው መነጋገራቸውን አረጋግጠው፣ ባለሥልጣናቱን ያስቆጣው ማስታወቂያ ምንም ችግር እንደሌለበት ተናግረዋል።

“በቅርቡ በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛ የለቀቅናቸውና በምርጫ ወቅት ሰላም እንዲኖር የጠየቅንባቸው ማስታወቂያዎች፣ አሁንም ተገቢ ናቸው፤ ብለን እናምናለን። ገለልተኛ እና ፖለቲካዊ ያልኾነው መልዕክት፣ የዚምባቡዌ የሥነ ጥበብ ባለሞያዎችን ሥራዎች የሚያንጸባርቁና ወጣቶች በምርጫ ወቅት ሰላም አስፈላጊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ የሚጠይቁ ናቸው።

ምርጫ የዴሞክራሲ ሒደት ዋና አካል ነው። ሁሉም ዝምባብዌያውያን፣ በተረጋጋ ኹኔታ መሪያቸውን የመምረጥ መብት አላቸው። ዩናይትድ ስቴትስ፣ የትኛውንም ዕጩም ይኹን ፓርቲ አትደግፍም። እኛ የምንደግፈው፥ ዚምባብዌያውያን፣ መሻታቸውን የሚገልጹበት ሰላማዊ እና ግልጽነት የሚታይበት ሒደት እንዲኖር ነው። ኤምባሲያችን፥ ሰላማዊ፣ ግልጽ እና ሁሉን አቃፊ ኹኔታ በዚምባብዌ እንዲኖር መወትወቱን ይቀጥላል።”

በዚምባብዌ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጥናት ክፍል ሓላፊ አሌክሳንደር ሩሴሮ እንደሚሉት፣ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፣ የአሜሪካው ጉዳይ አስፈጻሚ እንዲጠሩ ማድረጋቸው፣ “ትክክለኛ ውሳኔ ነው።”

“አንድ ኤምባሲ በአንድ አገር ውስጥ የሚገኘው፣ የአገሩን ፍላጎት በጠበቀ ኹኔታ ለመሥራት ነው። በአገሩ የውስጥ ጉዳዮች ለመግባትም መጨነቅ የለበትም። ስለዚኽ፣ በአሜሪካውያኑ ምክንያት የሚበላሽ ግንኙነት የለም፤ ምክንያቱም፣ አሜሪካውያኑ፥ ዲፕሎማሲ ምን እንደኾነ ያውቃሉ።”

በመጪው ነሐሴ እንደሚደረግ የሚጠበቀውን ምርጫ በተመለከተ፣ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ፣ እስከ አሁን ቀን አልቆረጡለትም።

ኮሎምበስ ማቩንጋ ከሐራሬ የላከውን ዘገባ ነው፡፡

XS
SM
MD
LG