በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የአዲስ ፕሬዚዳንትና ምክትል ሹመት ፀደቀ


ላለፉት አራት ዓመታት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት መዓዛ አሸናፊ እና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ። /ፎቶ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ገፅ/
ላለፉት አራት ዓመታት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት መዓዛ አሸናፊ እና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ። /ፎቶ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድቤት ገፅ/

መዓዛ አሸናፊና ምክትላቸው ሰሎሞን አረዳ በፍቃዳቸው መልቀቃቸው ተነግሯል።

ላለፉት አራት ዓመታት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት መዓዛ አሸናፊ እና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ በፍቃዳቸው ከኃላፊነት መነሳታቸው ታወቀ።

ተተኪዎቻቸውን ለመሾም ዛሬ ጥር 9/2015 ዓ.ም በተጠራው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ሁለቱም ባለስልጣናት ሥራቸውን የለቀቁት “በፍቃዳቸው” መሆኑን አስታውቀዋል።

በምትካቸውም አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ከበደ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢ አለ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በተወካዮች ምክር ቤት ተሹመዋል፡፡

ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፕሬዚዳንትነት የተሾሙት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ቃለ መሀላ ሲፈፅሙ። /ፎቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገፅ/
ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፕሬዚዳንትነት የተሾሙት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ቃለ መሀላ ሲፈፅሙ። /ፎቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገፅ/

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት አቅርበዋቸው በሦስት ድምፀ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ከበደ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በተለያዩ ሕግ ነክ ጉዳዮች ላይ ሲሠሩ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ በቀረበው የሕይወት ታሪካቸው ላይ እንደተመለከተው፣ አዲሱ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ በተለያዩ ባንኮች በነገረ ፈጅነት እና በሕግ ክፍል ኃላፊነት አገልግለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በሕግ አገልግሎት ክፍል ኃላፊነት እና የህግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰርነት አገልግለዋል፡፡ ለተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተቋማት በጥብቅና እና በሕግ ማማከር ዘርፍ እንዳገለገሉም ተብራርቷል፡፡

ተሿሚው በዳኝነት ዘርፍ ያላገለገሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ፣ “የዳኝነት ልምድ የሌለው ሰው እንዴት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት ሊሾም ቻለ” በሚል ከአንድ የምክር ቤት አባል ጥያቄ ተነስቷል፡፡

አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ለጥያቄው በሰጡት ምላሽ “ሹመቱ በአዋጅ በተቀመጠው መንገድ ሕጉን ጠብቆ የተፈፀመ ነው” ብለዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በዕጩነት የቀረቡት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሙሉ ድምፅ ሹመታቸው ፀድቋል፡፡

ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሾሙት ወይዘሮ አበባ እምቢ ቃለ መሀላ ሲፈፅሙ። /ፎቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገፅ/
ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በምክትል ፕሬዚዳንትነት የተሾሙት ወይዘሮ አበባ እምቢ ቃለ መሀላ ሲፈፅሙ። /ፎቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገፅ/

ወ/ሮ አበባ ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ ከአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጀምሮ በዳኝነት ስለማገልገላቸው በሥራ ልምዳቸው ላይ ተጠቅሷል፡፡ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አሁን

በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲመሩት በተሸሙበት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት እያገለገሉ እንደነበረም ተገልጿል፡፡

ሁለቱም ተሿሚዎች በሕዝብ ተወካዮች ፊት ቀርበው ቃለ መሐላ በመፈፀም ኃላፊነታቸውን ተቀብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ በነበረው የሹም ሽረት ሂደት ወደ ከፍተኛ ኃላፊነት ከመጡ አመራሮች መካከል የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ከጥቅምት 22/2011 ዓ.ም ጀምሮ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡

ወ/ሮ መዓዛም ሆኑ ምክትላቸው በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ከመገለጹ ባለፈ፣ የተነሱበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን በግልፅ የተባለ ነገር የለም፡፡

በሴቶች መብት ታጋይነቷ፣ የሕግ ነክ ጥያቄዎቻቸውንም ወደፊት በማምጣትና ሀገራዊ አጀንዳ እንዲሆኑ በማድረግ የምትታወቀውና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መስራች ከሆኑ ሴት የሕግ ባለሙያዎች መካከል የነበሩት ወ/ሮ መዓዛም ቢሆኑ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነታቸው ስለለቀቁበት ምክንያት እስካሁን የገለጹት ነገር የለም፡፡

ባለሥልጣናቱ ሥራ መልቀቃቸው ምክኒያት ምን እንደሆነ ከአሜሪካ ድምፅ የተጠየቁት አቶ ሰለሞን አረዳ በጉዳዩ ላይ የተናጥል ቃለ ምልልስ እንደማይሰጡ ገለፀው በነገው ዕለት በጋራ መግለጫ እንደሚሰጡ ገልፀዋል።

የወ/ሮ መዓዛ እና የምክትላቸው ከሥራ መልቀቅ የተገለጸው፣ አራት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት “መሸኘታቸው” ከተነገረ ከሦስት ቀናት በኋላ ነው፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 6/2015 ዓ.ም፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞግስ፣ የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ፣ የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ተፈሪ ፍቅሬ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት መሸኘታቸው ይታወሳል፡፡

ሸኝት ከተደረገላቸው ባለሥልጣናት መካከል አቶ ኡመር ሁሴን እና አቶ ተፈሪ ፍቅሬ በቅርቡ በአምባሳደርነት ከተሸሙት መካከል ሲሆኑ የወ/ሮ ዳግማዊት ሞግስ እና የአቶ ታከለ ኡማ ቀጣይ ጉዞ አልታወቀም፡፡ ሽኝት በተደረገላቸው ሚኒስትሮች ምትክ፣ እስካሁን የተሾመ አዲስ ባለሥልጣን የለም፡፡

XS
SM
MD
LG