በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሙስሊሞች ‘ድምፃችን ይሰማ’ ሲሉ የአንድ ዓመት መታሰቢያ አደረጉ


መስጂድ
መስጂድ

“ድምፃችን ይሰማ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረቡበትን አንደኛ ዓመት በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሰሞኑን አስበዋል፡፡




please wait

No media source currently available

0:00 0:21:41 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ


“ድምፃችን ይሰማ” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት ለመንግሥት ጥያቄ ያቀረቡበትን አንደኛ ዓመት በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሰሞኑን አስበዋል፡፡

ዕለቱን ዓርብ ጥር 10 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባና በሌሎም አካባቢዎች በተከናወኑ ሥርዓቶች ማሰባቸው ታውቋል፡፡

“ሠላማዊው ትግላችን የተጀመረበት አንደኛ ዓመት ነው” በሚል ሰሞኑንም በተለያዩ ከተሞች ውስጥ የሚስሊሙ ማኅበረሰብ አባላት የተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶችን ማካሄዳቸውን ከአዲስ አበባ ከሐረርና በደሴ ከተሞች ያነጋገርናቸው ምዕመናን አመልክተዋል፡፡

አዲስ አበባ ላይ ምዕመናኑ ያለፈውን ሣምንት ያሣለፉት እሥር ቤት የሚገኙትንና ቤተሰቦቻቸውን በመጠየቅ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡

ሐረር ከተማ ውስጥ “365 ቀናት ለሃይማኖት ነፃነት” በሚል ርዕስ የተሠናዳ ሥነ-ሥርዓት በኢማን አራተኛ መስጊድ ከተከናወነ በኋላ በተፈጠረ ሁኔታ መካከል አንድ በዚያ ሲያልፍ የነበረ ሕፃን በጥይት ተመትቶ መሞቱንና እናቱም መቁሰሏን የሚናገር ጥቆማና ዜና ደርሶናል፡፡ ሰሞኑንም የሐረሪ ፖሊስ ሁለት ወጣቶችን ከአዲስ አበባ ይዞ መውሰዱና ማሠሩም ተሰምቷል፡፡

ሁኔታውን ከሐረሪ ፖሊስ ለማጣራት ብዙ ሙከራዎችን ብናደርግም የሐረሪ ፖሊስ መልስ ለመስጠት ፍቃደኛ ወይም ዝግጁ ሣይሆን ቀርቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በደሴው ሸዋበር መስጊድም እንዲሁ የተቃውሞ ሥነ-ሥርዓት መካሄዱንና አማኒያንና ኢማሞችን ጨምሮ የታሠሩም ሰዎች መኖራቸውን የሚናገር ጥቆማ ሰምተናል፡፡

ሁኔታውን ለማጣራት ወደ ደሴ ፖሊስ ደውለን በቢሯቸው ያገኘናቸው ሳጅን ቸርነት ተፈጠሩ የተባሉት ሁኔታዎች ሁሉ “ያልነበሩ ናቸው” ሲሉ አስተባብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የደሴ ከተማ የአስተዳደርና የፀጥታ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ በላይ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ችግር መኖሩን እርግጥ ነው ብለው “አክራሪዎች ናቸው” ያሏቸው ሰዎች ኢማሞችን እንደሚጋፉ፣ የሶላትና የፀሎት ሥርዓቶችን እንደሚረብሹና መናገሪያዎችን እንደሚገነጣጥሉ፣ “ከመካከላቸው ነው” ያሉትም አንድ ሰው ሌላ ሰው በጩቤ ወግቶ ጉዳዩ በሕግ የተያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጥያቄአቸውን ለመንግሥት ያቀረቡት የሙስሊሙ ማኅበረሰብ አባላት ትግላቸው ሰላማዊ መሆኑን በየአጋጣሚው ይናገራሉ፡፡

በዋሽንግተን ዲሲና በአካባቢው ያሉ ሙስሊሞችና ደጋፊዎች የሚካፈሉበትን የፊታችን ጥር 18 ወይም ጃንዋሪ 26 የሚካሄድ አንድ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ፈርስት ሂጅራ የሚባለው ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚገኝ ተቋም አስታውቋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ሙስሊሞች ዓርብ ጥር 10 ቀን የዋለውን የከተራ በዓል ምክንያት በማድረግ “…ዕለቱ የክርስቲያን ወገኖቻችን በዓል በመሆኑ አንዋር መስጂድ አቅራቢያ በሚገኙ ቤተክርስቲያኖች ሊኖር የሚችለውን ዝግጅት ታሣቢ በማድረግ በአዲስ አበባ ፕሮግራሙ በኑር (በኒ) መስጂድ የሚከናወን ሲሆን በየክልሎችም አመቺ በሆኑ መስጂዶች ላይ ይከናወናል፡፡” የሚል መልዕክት ቀደም ሲል በትነው የፀሎቱንና “ድምፃችንን እናሰማለን” ያሉበትን ቦታ ለውጠዋል፡፡

ዝርዝሩን ያዳምጡ፡፡
XS
SM
MD
LG