በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በታዳጊው መርከብ 600 ፍልሰተኞች ከሥጥመት ተረፉ


በታዳጊው መርከብ 600 ፍልሰተኞች ከሥጥመት ተረፉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:06 0:00

"ድንበር የለሽ ሐኪሞች" የተባለው የሕክምና ገባሬ ሠናይ ቡድን፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ በጣሊያን ሲሲሊ አቅራቢያ ያሠማራው መርከብ፣ ወደ ስድስት መቶ የሚደርሱ ፍልሰተኞች፣ በአደገኛ ኹኔታ ይጓዙበት ከነበረ ጀልባ ላይ መታደጉ ተገለጸ፡፡

በአሕጽሮቱ (MSF) ተብሎ የሚጠራው "ድንበር የለሽ ሐኪሞች" ቡድኑ፣ በትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ "ጂዎ ባሬንት" የተባለው የትድግና መርከቡ፣ ፍልሰተኞቹ ተጨናንቀው ይጓዙበት ወደነበረው ጀልባ አቅጣጫ ያመራው፣ ከጀልባዋ የድረሱልን ጥሪ ከተላለፈለት በኋላ ነው፡፡

የገባሬ ሠናይ ቡድኑ መርከብ፣ ከጣሊያን መንግሥት በተሰጠው መመሪያ መሠረት፣ ፍልሰተኞቹን፥ ባሪ ወደተባለው የደቡባዊ ጣሊያን ወደብ ይዞ እየቀዘፈ እንደኾነ ሲያስታውቅ፣ ጉዞው ወደ አርባ ሰዓታት ገደማ እንደሚወስድ ጠቁሟል፡፡

ሕገ ወጥ ፍልሰትን በሚመለከት፣ ጥብቅ ፖሊሲ የሚከተለው በጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ መሎኒ የሚመራው የጣሊያን መንግሥት፣ ባሕር ላይ በአደገኛ ኹኔታ ሲጓዙ የሚታደጋቸውን ፍልሰተኞች፣ ኾነ ብሎ ከተገኙበት ሥፍራ ርቆ ወደሚገኝ ወደብ በተደጋጋሚ እንዲወሰዱ ያደርጋል፤ በማለት ገባሬ ሠናይ ድርጅቶች እና ሌሎችም መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ነቀፌታ ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡

እ.አ.አ በዘንድሮ 2023 እስከ አሁን ባለው ጊዜ፣ ከ47ሺሕ የሚበልጡ ፍልሰተኞች፣ ወደ ጣሊያን ምድር መድረሳቸው ተነግሯል፡፡ የጣሊያን የአገር ግዛት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፣ ባለፈው ዓመት፣ በዚኹ ተመሳሳይ ጊዜ የገቡት፣ 18ሺሕ ገደማ ነበሩ፡፡

XS
SM
MD
LG