በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተጠቆመ


በተለያዩ ሃገራት ከሚያገለግሉትና ለሥልጠና ከመጡት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች የተወሰኑት በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ታማኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል።

በቫይረሱ መያዛቸው የተነገራቸው አምባሳደሮች ቁጥር ይሄን ያህል ነው ማለት እንደማይቻል የጠቀሱት ምንጮቹ፣ የተነገራቸው በየግል በመሆኑ ድምሩን ማስቀመጥ እንደማይቻል አመልክተዋል። ቀደም ሲል ሲጠቀስ የነበረው ቁጥር ግን 12 እንደነበር ነው የጠቆሙት፤ ቆየት ብለው የወጡ ያልተረጋገጡ መረጃዎች ደግሞ 21 አድርሰውታል::

ሁኔታውን ለስልጠና ከመሰባሰባቸው ጋር ማገናኘት እንደማይቻል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምንጮች አክለው ጠቅሰዋል።

ከየትኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ናሙና ሲወሰድ እንደሚሆነው ሁሉ ከአምባሳደሮቹም መካከል የተወሰኑት ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል ነው ያሉት።

ከተለያየ የዓለም ክፍል መጥተው ለተሰባሰቡ ሰዎች ምርመራ ሲደረግ በቫይረሱ የተያዙ መገኘታቸው የሚጠበቅ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

አምባሳደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በቢሾፍቱ ከተማ ኩሪፍቱ መዝናኛ በተካሄደው ስልጠና ለመሳተፍ መሆኑንም የቪኦኤ ዘገቢ እስክንድር ፍሬው ያደረሰን ዘገባ ያመለክታል።

XS
SM
MD
LG