በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ የስዊድን ኢምባሲዋን ልትዘጋ ነው


ጠቅላይ ሚኒስር መለስ መንግስታቸው ከስዊድን ጋር የጠበቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሌለው ይናገራሉ
ጠቅላይ ሚኒስር መለስ መንግስታቸው ከስዊድን ጋር የጠበቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንደሌለው ይናገራሉ

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመጭው ጥቅምት አካሂዳለሁ ባሉት የመንግስት ለውጥ፤ እየተቀያየረ የሚሄደውን የኢትዮጵያን የወዳጅነት አቅጣጫ ተከትለው የሚዘጉና አዲስ የሚከፈቱ ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮኖች እንደሚኖሩ አስታወቁ።

ከሚዘጉት መካከል የመጀመሪያ የሚሆነው በስዊድን የኢትዮጵያ ኢምባሲ እንደሚሆን ተናግረዋል።

"በኛና በስዊድን መካክል ትርጉም ያለው የልማት ትብብር መርሃ ግብርም ሆነ የንግድ ልውውጥ የለም፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ የጎላ ኢንቨስትመንትም የለም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ።

"ብራዚል ወደ ብልጽግናው አለም እየዘለቀች ያለች ግዙፍ አገር ሆና በዚያ ግን ኢምባሲ የለንም። ስለዚህ የስዊድን ኢምባሲያችን ከሚዘጉት ቀዳሚው ነው። ምክንያቱም ኤምባሲ በዚያ መክፈት ጥቅም ያለው ጉዳይ አይደለም፣" ብለዋል።

በዩናይትድ ስቴትስና በኢትዮጵያ መካከል ያሉት ግንኙነቶች ለወራት በውጥረት ውስጥ ከቆዩ በኋላ አሁን እየተጠገኑ ነው ሲሉ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ፡፡

ያ ከዋሽንግተን ጋር በአስቸጋሪ ሁኔታ የተወጠረ ያሉት የግንኙነት ሁኔታ ዛሬ ያለፈ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አመልክተዋል፡፡

"ባለፉት ስድስት እና ሰባት ወራት ገብተንበት የነበረው አስቸጋሪ መካረር በብዙ ርቀት ወደኋላ የቀረ ይመስለኛል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት በተለየ ሁኔታና አክብደው የሚያይዋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በእነዚያ በማንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ላለመስማማት እንስማማለን፤ የጋራ ጥቅሞቻችንን በሚያገለግሉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ አብረን ለመሥራት እንስማማለን፡፡" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

ለአንድ ዓመት ክፍት ሆኖ የቆየው በዩናይትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ አምባሣደር ቦታም በመጭው ጥቅምት ወር አጠቃላይ ለውጥ አድርገው አዲስ መንግሥት ሲመሠርቱ በሚሾም አምባሣደር እንደሚሞላ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጠቁመው የካቢኔ ለውጡ የሃገሪቱን የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖችም እንደሚያጠቃልል ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ ይፋ ስለተደረገው የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ ሲናገሩም የሃገሪቱ የውጭ የምግብ ዕርዳታ ጥገኝነት እንዲያበቃ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጠቁመው በተባለው ጊዜ ኢኮኖሚው ከ11 እስከ 14 ከመቶ የሚደርስ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG