የዩናይትድ ስቴትስ ዋና ከተማ ዋሺንግተን ዲሲና ሃምሳውም ግዛቶች በመቶዎች ሺሆች የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን ዛሬ አስተናግደዋል።
የሰልፉ መሪ ርዕስ “ለሕይወታችን እንሰለፍ” የሚል ሲሆን የጦር መሣሪያዎችን በመያዝ አሠራር ላይ የጠበቀ ቁጥጥር እንዲደረግ የሚጠይቁ ሰልፈኞች ናቸው በየአደባባዩ የወጡት።
በዋሺንግተን ዲሲው ሰልፍ ላይ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ተማሪዎች፣ ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸው ይወጣሉ ተብሎ ቀደም ሲልም ተገምቶ የነበረ ሲሆን በሁሉም የአሜሪካ ስቴቶች ውስጥ ወደ ስምንት መቶ የሚሆኑ ተመሣሣይ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በትምህርት ቤቶች፣ በመዝናኛ ሥፍራዎች፣ በሥራ ቦታዎችና በሌሎችም ሥፍራዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ተኩስ በሚከፍቱ ሰዎች በቀን በአማካይ የዘጠና ስድስት ሰው ሕይወት እንደሚጠፋና በዓመት ከሰላሣ ሺህ ሰው በላይ ከጦር መሣያዎች ጋር በተያያዙ ጥቃቶች ወይም እርምጃዎች እንደሚገደል ወይም እንደሚሞት በቅርቡ የወጡ አኀዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ።
ታኅሣስ 6/1783 ዓ.ም. /በኢት.የዘ.አ./ የፀደቁት የዩናይትድ ስቴትስ ሕገመንግሥት የመብቶች ድንጋጌዎች አካል የሆነው ሁለተኛው ማሻሻያ መሣሪያ በንብረትነት የመያዝና ይዞም የመንቀሳቀስ መብትን የሚያረጋግጥ ሲሆን በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የበረታ ተፅዕኖ እንዳለው የሚታወቀው ብሔራዊ የነፍጥ ማኅበር /ኤንአርኤ/ ይህንን ድንጋጌ እንደሚጠብቅ ይናገራል።
https://www.voanews.com/a/march-for-our-lives/4314353.html
የዩናይትድ ስቴትስ ሕገመንግሥት መሣሪያ በንብረትነት የመያዝና ይዞም የመንቀሳቀስ መብትን ያረጋግጣልየዩናይትድ ስቴትስ ሕገመንግሥት የመብቶች ድንጋጌዎች አካል የሆነው ሁለተኛው ማሻሻያ - ታኅሣስ 6/1783 ዓ.ም. /በኢት.የዘ.አ./
146 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረውና አምስት ሚሊየን አባላት እንዳሉት የሚነገረው ኤንአርኤ በጦር መሣሪያ ባለቤትነት ጉዳዮች ላይም የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ቁጥጥር ይቃወማል።
ኤንአርኤ ምንድነው? ከላይ የተያያዘውን ማገናኛ ሲከተሉ የሚያብራራ የቪድዮ ፋይል ያገኛሉ።
አሜሪካዊያን በጦር መሣሪያ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ያላቸው አመለካከት በየወቅቱ እየተቀያየረ የመጣ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ወደ ስድሣ ዘጠኝ ከመቶ የሚሆኑ የሃገሪቱ ዜጎች በጦር መሣሪያ ባለመብትነት ጉዳይ ላይ ጠበቅ ያሉ ቁጥጥሮች እንዲደረጉ የሚፈልጉ መሆናቸውን የአሶሺየትድ ፕሬስ የሕዝብ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል ያደረገው ቅኝት አሳይቷል።
በጥቅምት 2005 ዓ.ም ይህ መጠን 55 ከመቶ የነበረ ሲሆን ባለፈው ዓመት ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ደግሞ ወደ 61 ከመቶ ከፍ ብሎ እንደነበረ ይኸው ጥናት አመልክቷል።
ስድሣ ዘጠኝ ከመቶ የሚሆኑ አሜሪካዊያን በመሣሪያ ባለመብትነት ጉዳይ ላይ ጠበቅ ያሉ ቁጥጥሮች እንዲደረጉ ይፈልጋሉአሶሼትድ ፕሬስ - የሕዝብ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል አዲስ ቅኝት
ይህንን ዓይነት የጠበቀ ቁጥጥር እንዲደረግ ከዴሞክራቶቹ ዘጠና ከመቶ፣ ከሪፐብሊካኑ ሃምሳ ከመቶ፣ ከመሣሪያ ባለቤቶች ደግሞ 54 ከመቶ የሚሆኑት እንደሚደግፉ ተገልጿል።
በሰልፉ ላይ ልጆቹን ይዞ ወጥቶ የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገር “አሜሪካ እኮ ጦርነት ውስጥ ያለች ሃገር አይደለችም፤ ይሄ ሁሉ መሣሪያ ለሰዉ ለምን እንደሚሸጥ አይገባኝም፤ እራስን ለመከላከል ሽጉጥ ይበቃል፤ አውቶማቲክ ጠብመንጃ ወታደር ጋ ካልሆነ ሰው እጅ ውስጥ ምን ያደርጋል?” ብሏል።
ዩናይትድ ስቴስት ውስጥ ከጦር መሣሪያዎች ጋር በተያያዙ ጥቃቶችና የሁከት አድራጎቶች በማንኛውም መደበኛ ቀን ሰባት ሕፃናትና ዕድሜአቸው በአሥራዎች ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች ይረግፋሉ።
ዛሬ የተካሄዱትን ሰልፎች ያዘጋጁትና የመሩት፣ በየመድረኮቹም ንግግሮችን ያደረጉት ዕድሜአቸው በአሥራዎቹ ውስጥ የሆኑ ተማሪዎችና ታዳጊዎች ናቸው።
በቅርቡ 17 ተማሪዎችና መምህራን በአንድ አደጋ ጣይ የተገደሉበት የፓርክላንድ-ፍሎሪዳው ማርጆሪ ስቶንማን ደግላስ ትምህርት ቤት ተማሪ ዴቪድ ሆግ ንግግር፤ ከታች ያለውን ማገናኛ ይከተሉ
https://www.voanews.com/a/march-for-our-lives/4314722.html
ይህ በጦር መሣሪያ ላይ የሚደረግ ቁጥጥር ጉዳይ ከሰባት ወራት በኋላ በሚካሄዱት የአማካይ ዘመን የተወካዮች ምክር ቤት፣ የስቴቶችና የአካባቢ ሥልጣናት ምርጫ ወቅት የጎላ ቦታ ይኖረዋል ተብሎ እየተነገረ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በሲቪሎች እጆች ውስጥ ከ280 ሚሊየን በላይ የጦር መሣሪያዎች እንዳሉ ሠነዶች ይጠቁማሉ።
"ለሕይወታችን እንሰለፍ" ከሥር ያለውን ማገናኛ ተከትለው የፎቶ መድብል ይመልከቱ፤ በዩናይትድ ስቴትስና በሌሎችም የዓለም ከተሞች የተደረጉ ትጥቅን የሚቃወሙ ወይም የበለጠ ቁጥጥር የሚጠይቁና ትጥቅን የሚደግፉ ሰልፎችን ያያሉ
https://www.voanews.com/a/4314488.html
አሜሪካ ውስጥ በመሣሪያ ምክንያት የሚፈፀመው የግድያ መጠን በሌሎች የበለፀጉ ሃገሮች በዓመት ከሚደርሰው አማካይ በሃያ አምስት ጊዜ የገዘፈ መሆኑን፣ በሕዝብ ብዛት ዩናይትድ ስቴትስ 46 ከመቶውን ድርሻ ብትይዝም በሁከት አዘል ሞት ደግሞ 82 ከመቶ የሚሆነው ጉዳት እንደሚደርስባት ይነገራል።
የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ
የተያያዙ ማገናኛዎችን እየተከተሉ ከሠልፉ ላይ የተቀረፁ ቪድዮ ፋይሎችንና ፎቶዎችን ይመልከቱ
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ