በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"የጠፉት ልጆች"


በኢትዮጵያ ያሉ ሱዳናዊያን ወጣቶች ለውሣኔ ሕዝቡ እየተዘጋጁ ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ዘመን ከሃገራቸው የወጡ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ዘጎች የፊታችን ጥር 1 ቀን ለሚካሄደው የደቡብ ሱዳን የነፃነት ውሣኔ ሕዝብ ድምፃቸውን በያሉበት ለመስጠት በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡

አዲስ አበባ የሚገኘው ሪፖርተራችን ፒተር ሃይንላይን እዚያ በተቋቋመ የምዝገባ ጣቢያ ላይ አንድ ሱዳናዊ ወጣት አግኝቶ አነጋግሯል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ወላጆቻቸውን ካጡ ሕፃናት አንዱ ነው፡፡ እነዚያ ሕፃናት "የጠፉ ልጆች" በሚል የወል ስም ይታወቃሉ፡፡ ፒተር ያነጋገረው ወጣት የአዲስ አበባውን የምዝገባና የምርጫ ዘመቻ ይመራል፡፡

ኒኻል አሲየክ ዴቪድ ስለደቡብ ሱዳን ያለው ትውስታ የደበዘዘ የልጅነት ትውስታ ነው፡፡ ጊዜው የዛሬ ሃያ አንድ ዓመት የጦርነት ዘመን ነበር፡፡ ያኔ ኒካል የሰባት ዓመት ጨቅላ ነው፡፡ ሕፃናቱ በዚያ ዓይነትና ባነሰም ዕድሜአቸው ከወላጆቻቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ለመለያየት ተገድደዋል፡፡ እናም እርሱ በዚያ የፍዳና የስደት ዘመን ወደምሥራቅ ከተጓዙት ማረፊያ ቤታቸውም ኢትዮጵያ ከሆነችላቸው ቡድኖች መካከል ተገኘ፡፡

"የእሣት ነበልባል አየሁ፤ ለመራመድ እራሴን የምችል አልነበርኩም፡፡ ብዙ ሰዎች አብረውኝ ነበሩ፡፡ ይሸከሙኝ ነበር፡፡ ወደየት መሄድ እንዳለብኝ አላውቅም ነበር፡፡ ብዙ ቁጥር ያለው ሰው ግን ዝም ብሎ ይጓዝ ነበር፡፡ ይሄው እስከአሁን ወደቤተሰቤ አልተመለስኩም፡፡" አለ ዴቪድ፡፡

ይህ የሆነው የዛሬ ሃያ አንድ ዓመት ነበር፡፡ ዛሬ ዴቪድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቱ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር - ዩኤንኤችሲአር የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሆኖ የኮሌጅ ተማሪ ነው፡፡ ጥር አንድ ቀን ለሚካሄደው የደቡብ ሱዳን መገንጠል ወይም አንድነት ውሣኔ ሕዝብ ድምፅ አሠጣጥ የአዲስ አበባውን የምዝገባ ማዕከል ይመራል፡፡

ያ ለሃያ አንድ ዓመታት የዘለቀ ጦርነት የሁለት ሚሊየን ሱዳናዊያንን ሕይወት እንደበላ ይነገራል፡፡ ጦርነቱ የቆመው ታዲያ የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ በተፈረመው አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ነው፡፡ ስምምነቱ ሲፈረም ከአንጓዎቹ አንዱ ይህ ልክ የዛሬ ወር የሚካሄደው ውሣኔ ሕዝብ ሊደረግ ተቋጥሮ ነበር፡፡

እነዚያ በምድር ላይ ሁሉ የተበተኑ የርሱ ትውልድ ልጆች እንግዲህ ከያሉበት መሰብሰባቸው፣ በሕይወት ከተረፉ ዘመድ አዝማዶቻቸውም ጋር እንደገና መቀላቀላቸው የዘወትር ሕልሙ እንደሆነ ሚኻል ዴቪድ ሲናገር እንዲህ አለ፡፡

"ጦርነት ታክቶናል፡፡ ለምን ደቡብ ሱዳን የራሷ ነፃ መንግሥት አይኖራትም? ሉዓላዊ ሃገር መሆን፣ እንደሌሎቹ አፍሪካዊያን ወገኖቻችን የራሣችንን መብቶች መጠቀም፣ የራሣችንን ሕይወት መኖር፤ ይህ በመላው ዓለም እንዳሉት ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ሱዳናዊያን ወጣቶች አቋም ነው፡፡"

ሌላው ዱዝ ዴንግ ጎት "ከጠፉት ልጆች" አንዱ ነው፡፡ ደረቱ ላይ "የመራጭ ምዝገባ ኃላፊ - ቀጣና አራት" የሚል ባጅ ለጥፎ በኩራት ይንጎማለላል፤ በሰባት ዓመት ዕድሜው ወደኢትዮጵያ ምድር ያጋጠመውን ስደት እያወጋ፡፡

"ቤተሰቦቼን ያጣኋቸው በኢትዮጵያና በሱዳን ወሰን ላይ የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር - የሚለው ጎት ወደ ስደተኞች ሠፈር ሄድኩና ስደተኛ ልጅ ሆኜ መኖር ጀመርኩ፤ በአንድ ቦታ ተሰብስበን የምንኖር 36 ልጆች ነበርን፡፡ እዚያ ስንኖር የማገዶ እንጨት እንለቅማለን፤ ምግብ ዩኤንኤችሲአር ይሰጠናል፡፡ ይበልጥ የከበዱ ችግሮች ሲያጋጥሙን ከጓደኞቼ ጋር ሆነን እንጋፈጣቸዋለን፡፡ በዚያ መሃል የሞቱም አሉ፡፡ ሁሉም ነገር እንዲህ ሆኖ ያለቤተሰብ ቀረሁ፡፡" ብሏል፡፡

ጎት አሁን የሃያ ስድስት ዓመት ወጣት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቋል፡፡ ከሁለት ሺህ አምስቱ ስምምነት በኋላ ግን ወላጆቹ ከጦርነቱ በሕይወት መትረፋቸውን መስማቱን ይናገራል፡፡ ያንን የትውልድ ቤተሰቡን አዲስ አበባ ላይ ከመሠረተው አዲስ ቤተሰብ ጋር ስለሚያገናኝበት ቀን ይፀልያል - ጎት፡፡

ከወንድሞቹ አንዱ በስደተኞች ሠፈር እያለ ሊፈልገው ሄዶ እንደነበርና ዲማ በሚባለው ጣቢያ በሕይወት እንዳገኘው፤ ከዚያም ወደሱዳን ወስዶት ቤተሰቦቹ፡፡ በሕይወት እንዳሉ ማወቁን ተናገረ፡፡ አሁን ጎት ትዳር አለው፡፡ የሁለት ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነው፡፡

ጎት ይህንን ታሪኩን ለፒተር እያወራለት ሣለ፤ ሁለት ሴቶች ሊመዘገቡ መጡ፡፡ የሃያ ስምንት ዓመቷ ንያብዩ ኮንግ በጦርነቱ ውስጥ ለተገደሉባት የቤተሰቧ አባላት ክብር እንደሆነ ድምጿን የምትሰጠው ትናገራለች፡፡

"አባቴ ወታደር ነበር፡፡ ለደቡብ ሱዳን ሲዋጋ ተገደለ፡፡ ወንድሞቻችን፣ ዘመዶቻችን ለዚያ ምድር ሲሉ ለረጅም ዓመታት ተዋግተው ሕይወታቸውን ሰጥተዋል፡፡ እናም ለእነዚያ ሰዎች ሕይወት ክብር ስል ድምፄን ለደቡብ ሱዳን እሰጣለሁ፡፡" አለች ኮንግ፡፡

'አርባ አምስት ሺህ' ለምትላቸው የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ኢትዮጵያ መጠጊያና መጠለያ በመስጠቷ ምሥጋና አቀርባለሁ' ትላለች ኮንግ፣ ብዙዎቹ በዚያ ከሃያ ዓመታት በላይ ኖረዋል፡፡ የስደት ሕይወታችንን በመውደዳችን ምክንያት እዚሁ መቅረት አንፈልግም፤ የመጣው ይምጣ እንመለሣለን፡፡ ልጆቻችን በእናት ሃገራቸው ምድር ማደግ አለባቸው፡፡ - አለች ንያብዩ ኮንግ፡፡

የድምፅ ሰጭ ምዝገባው ኅዳር 29 ቀን ይጠናቀቃል፡፡ እናም የተመዘገቡት ጥር አንድ ቀን ከኻርቱም ጋር ለመለያየት ወይም በአንድነት ለመቀጠል ድምፃቸውን ሊሰጡ ወደዚሁ ጣቢያ ይመለሣሉ፡፡

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG