የአውሮፓ ሃገሮችና ባሕሩ ላይ የሚንቀሣቀሱ መርከቦች አዛዦች የስደተኞቹን ሕይወት እንዲታደጉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ጠየቀ፡፡
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ትብብር ድርጅት (ኔቶ) እና የአውሮፓ ሕብረት ደግሞ አፍሪካዊያኑን ሰደተኞች ለመርዳት የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡
የሊብያን ጦርነት እየሸሹ ሜዲቴራኒያን ባሕር ውስጥ በሚደርሱባቸው አደጋዎች የሚሞቱ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ እጅግ እያሣሰበው መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር (ዩኤንኤችሲአር) እየተናገረ ነው፡፡
እዚያ ያሉ ችግሮችን ከመጋፈጥ ይልቅ የባሕር ጉዞን በማይመጥኑ ጀልባዎች እየተሣፈሩ ለማምለጥ የሚመክሩት ሰዎች ከዕለት ወደዕለት እየበዙ ነው፡፡ ይህ መከራቸው ብዙ ጊዜ ተመልካች የለውም፤ ወይም መልስ አይሰጠውም ወይም ሲያልቁ ዝም ተብለው ይታያሉ፡፡
ባለፈው ዓርብ የደረሰው አሣዛኝ አጋጣሚ ለብዙ ስደተኞች ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ከትሪፖሊ ወደብ ተነስተው ሜዲቴራኒያንን ለማቋረጥ ጉዞ እንደጀመሩ በተሰበረች ጀልባ ውስጥ የነበሩ የአሥራ ስድስት ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል፡፡ ሁለቱ የሕፃናት ናቸው፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ግን ገና ብዙ የሰጠሙ ሰዎች አስከሬኖች ሊገኙ እንደሚችሉ ፍርሃቱን ተናግሯል፡፡
ስድስት መቶ የሚሆኑ ብዙዎቹ ሊብያ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞች አልያም ደግሞ ወደሊብያ ለሥራ ገብተው የነበሩና አመፁ በመቀስቀሱ ምክንያት መውጫ ያጡ አፍሪካዊያን ሠራተኞች በአንዲት ደካማ ጀልባ ውስጥ ተጠቅጥቀው ጉዞ እንደጀመሩ ተሰብራ ሰጥማለች፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት የጥሪውን አጣዳፊነት እንዲያውቁለት ለአውሮፓ መንግሥታትና በሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ለሚቀዝፉ መርከቦች አቤቱታ እያሰማ ነው፡፡ በባሕር ላይ ልማድ መሠረት ባሕረኞቹ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች እንዲደርሱላቸው ይገደዳሉ - ይላሉ የተባበሩት መንግሥታት ቃል አቀባይዋ ሜሊሳ ፍሌሚንግ፡፡ "ከሊብያ የሚነሣ ማንኛውም ጀልባ በመጀመሪያ እይታ እንኳ እርዳታ የሚፈልግ እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡ በመሠረቱ እነዚያ ጀልባዎች፣ ሁሉም፣ እንዲሁም በብጥብጡ ምክንያት የተዳከሙ ሰዎች የተሣፈሩባቸው ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ እባካችሁ የሰቆቃ ድምፅ እስክትሰሙ አትጠብቁ፡፡ እንለምናችኋለን፡፡ እባካችሁ፤ ወደ ጀልባዎቹ ሂዱ፣ እርዳታ ይፈልጉ እንደሆነ እዩ፤ ችግር ላይ ከሆኑ አድኗቸው፡፡" ሲሉ ጥሪያቸውን አሰምተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው 12 ሺህ 360 ስደተኞች ከሊብያ ተነስተው ጣልያንና ማልታ ገብተዋል፡፡ ከመጋቢት 16 ቀን ወዲህ ብቻ እንኳ ቢያንስ ስምንት መቶ የሚሆኑ ሰዎች የጠበቃቸው ቀና ጉዞ አልነበረም፤ ወደ ሰላሙ መጠጊያ አልደረሱም፡፡ ይህ ባለፈው ሣምንት የባሕር ላይ አደጋ ያጋጠማቸውን ስድስት መቶ ስደተኞች ሣይጨምር ነው፡፡
በተጓዦችና በባሕር ትራንስፖርት፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ቁጥራቸው እጅግ የበዛ መርከቦች በሚርመሰመሱበት በዚያ የሜዲቴራኒያን ባሕር መሥመር ላይ ለአደጋ ተጋልጠው የነበሩት የጀልባ ተጓዥ ስደተኞች ጨርሶ ሣይታዩ ሊቀሩ እንደማይችሉ የዩኤንኤችሲአር ቃልአቀባይዋ ፍሌሚንግ ተናግረዋል፡፡
"ሊብያ ውስጥ ባለው ግጭት ምክንያት በተጠናከረ ሁኔታ እየተቃኘ ያለ አካባቢ ነው፡፡ በመሆኑም ሌላ ሕይወት እንዳይጠፋ አንዳች ነገር መደረግ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ እኛ ባሕሩን የምናየው ሰዎች በሰላም አቋርጠው ከለላና ጥበቃ ሊያገኙበት እንደሚችሉት እንደማንኛውም ድንበር ነው፡፡ እንደ ቱኒዝያ፣ ወይም እንደግብፅ፡፡ ምናልባት ይህ መንገድ ከሊብያ የመሸሻ እጅግ አደገኛ ከሆኑ ማምለጫ ቀዳዳዎች አንዱ ነው፡፡" ብለዋል ሚስ ፍሌሚንግ፡፡
ደካማ በሆኑት የሕገወጥ አጓጓዦች ጀልባዎች ላይ ለመውጣት አደገኛ በሆነ ሁኔታ የሚወስኑት ደግሞ ብዙውን ጊዜ የብዝበዛና የመጎሣቆል ሰለባ እንደሚሆኑ ዓለምአቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) አመልክቷል፡፡
ስደተኞቹ ከሊብያ በባሕር ለማምለጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለሕገወጦቹ አስተላላፊዎች ይከፍላሉ፡፡ የሚገጥማቸው ግን እጅግ አሣሣቢ እየሆነ በሄደ ሁኔታ የተባላሸና አደጋ የበዛበት አያያዝ ነው፡፡ በየጊዜው እየተደጋገመ እንደሚያጋጥማቸው ንብረቶቻቸውን ይቀማሉ፡፡ ገንዘባቸውን፣ ሻንጣዎቻቸውን፣ ስልኮቻቸውን ... በእነዚያ ሕሊና ቢስና መታመን በሌላቸው አጓጓዦቻቸው ይዘረፋሉ፡፡
ችግር ከበዛባቸው ጀልባዎች ተርፈውና ከአደጋው ሁሉ አምልጠው ያንን የደህንነት ማረፊያ ለመድረስ የታደሉቱ አፍሪካዊያን ስደተኞች ያሰሙትን እሮሮና ብሶት ይዞ የወጣው የእንግሊዙ "ዘ ጋርዲያን" ጋዜጣ በባሕር ላይ በመከራ ውስጥ በነበሩበት ወቅት ያሰሟቸው የነበሩ የጣዕርና የድረሱልን ጥሪዎቻቸውን የአውሮፓ መንግሥታትና የኔቶ መርከቦች እያዩ ረግጠዋቸው ያልፉ እንደነበር መናገራቸውን ዘግቧል፡፡
የኔቶ ቃል አቀባይ ካርመን ሮሜሮ ግን የሚናገሩት ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የጦር ትብብር ድርጅታቸው ዋነኛ ዓላማ ሊብያ ውስጥ ሲቪሎችን ከአደጋና ከጥቃት መከላከል ቢሆንም በባሕር ላይም ቢሆን በችግር ላይ ላሉ እርዳታ እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ሮሜሮ በመቀጠልም "የኔቶ መርከቦች ያንን ኃላፊነታቸውን እየተወጡ በችግር ላይ ላሉ መርከቦችም ጥሪዎች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ ይህ የባሕር ላይ ሕግ የሚያዘን ግዴታችን ነው፡፡ የመርከቦቻችን ካፒቴኖች ከዚህ በተፃራሪ ፈፅመው ቢገኙ መልካም አድራጎት አይሆንም ክብር የጎደለውም ተግባር ነው የሚሆነው፡፡" ብለዋል፡፡
ሮሜሮ እንደማሣያም አንስተው በቅርቡ በሁለት ጀልባዎች ተሣፍረው የነበሩ አምስት መቶ ሰዎችን ማትረፋቸውን አመልክተው በቅርቡ ደግሞ በሊብያ መንግሥት በግዳጅ ጀልባ ላይ ተጭነው የነበሩ ሰዎች የተሣፈሩባት ጀልባ ብዙም ሣትርቅ መስጠሟን በመጠቆም ከስሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ፍሮንቴክስ በሚል ምህፃር የሚታወቀው የአውሮፓ ሕብረት የወሰን ጥበቃ መሥሪያ ቤት በባሕር ላይ የነበሩ ስደተኞችን ከአደጋ መታደጉን አንድ የሕብረቱ ቃልአቀባይ ተናግረዋል፡፡
በጣልያኗ ደሴት ላምፔዱሣ እንዲያርፉ ለተደረጉት ስደተኞች የተሰጠው ድገፍም የመርኃ ግብራቸው አካል መሆኑን ቃል አቀባዩ አመልክተዋል፡፡
"አውሮፓ እነዚህን ስደተኞች ማባረር ሣይሆን መቀበል ነው ያለባት" ብለዋል ትናንት ብራስልስ ላይ መግለጫ የሰጡት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አባል ዴቪድ ኒከላስ፡፡
"ሰዎች ወደ አውሮፓ እንዳይዘልቁ፣ የአውሮፓን ወሰኖች እንዳያቋርጡ ለመከልከል ሲባል ከአውሮፓ ለተራዘመ ጊዜ የምንሰማው ሁሉ የተጣመመና መሥመሩን ጨርሶውኑ የሣተ ነው፡፡ በችግርና በሥቃይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለመታደግ የሚደረግ አንዳች ነገር የለም፡፡" ብለዋል ኒከላስ፡፡
የእነዚህን አፍሪካዊያን ስደተኞች ጉዳይ ለመምከርና መፍትሔም ለመፈለግ የአውሮፓ ሕብረት ሚኒስትሮች በያዝነው ሣምንት መጨረሻ ላይ ይገናኛሉ ተብሏል፡፡
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡