በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩኤንኤችሲአር ሊብያ ስለሚገኙ ስደተኞችና የውጭ ዜጎች


ሲቤላ ዊልክስ፤ ዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ
ሲቤላ ዊልክስ፤ ዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ

ሊብያ ውስጥ ለሚገኙ በአሥር ሺሆች ለሚቆጠሩ ስደተኞችና የሌሎች ሃገሮች ዜጎች ያላቸውን ስጋት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር አንቶኒዮ ጉቴሬስ ዛሬ ገልፀዋል፡፡

ሰሎሞን አባተ ወደ ጄኔቫ ደውሎ የስደተኞቹን ሁኔታ አስመልክቶ የኮሚሽነሩን ቃል አቀባይ ሲቤላ ዊልክስን አነጋግሯል፡፡

በጦርነት ከደቀቁት ወይም እጅግ ድኃ ከሆኑት ከሠሃራ በስተደቡብ ከሚገኙ የአፍሪካ ሃገሮች ሄደው ሊብያ ውስጥ የሚገኙ የውጭ ዜጎችን የሚያወጣ መርከብም ሆነ አይሮፕላን የለም፡፡ እነዚያን ሰዎች ለመታደግ ጠንካሮቹ ሃገሮች የቻሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ፣ ለስደተኞቹም ለእራሣቸው ዜጎች የሚያደርጉትን ሁሉ እንክብካቤ እንዲያደርጉላቸውና ትኩረት እንዲሰጧቸው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር አንቶኒዮ ጉቴሬስ ጥሪ አሰምተዋል፡፡

እነዚያ ሰዎች በጥቃት ሥር እንዳሉ እንደሚሰማቸው ማሣወቃቸውንም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል፡፡ "ደህንነታቸው አደጋ ላይ ነው፡፡ ሊያቆያቸው የሚችል ቀለብም የላቸውም፡፡" ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡

ሊብያ ውስጥ ስምንት ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን፣ ኤርትራዊያን፣ ሶማሌያዊያን፣ ሱዳናዊያን፣ ፍልስጥኤማዊያንና ኢራቃዊያን ስደተኞች እንደሚገኙ ይኸው ዛሬ የወጣው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች መሥሪያ ቤት መግለጫ ይናገራል፡፡

ከስደተኞቹና ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ጋር እየተገናኙ እንደሆነና ለመገናኘትም ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይዋ ሲቤላ ዊልክስ ተናግረዋል፡፡

"ያሉበት ሁኔታ በጣም ያስጨንቀናል፤ ብዙዎቹ ከሠሃራ በስተደቡብ ካሉ የአፍሪካ ሃገሮች የመጡት ከፍተኛ ፍርሃት ላይ መሆናቸውን ነግረውናል፤ 'ቅጥረኞች ተብለን እንጠረጠራለን' የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ሁሉም አፍሪካዊያን ከመንግሥቱ ጋር የሚሠሩ ናቸው የሚል ወሬ ተናፍሷል፡፡" ብለዋል ሚስ ዊልክስ፡፡

ትሪፖሊ የሚገኙት የዩኤንኤችሲአር ሠራተኞች ስደተኞቹን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማገዝ እንደሚቻል መረጃ እየሠጧቸው እንደሆነ ሚስ ዊልክስ አመልክተዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት ቢያንስ ሁለት ኢትዮጵያዊያን መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ ዊልክስ ስለኤርትራዊያን ስደተኞች ሲናገሩ ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን፣ በተደብቀው እንደሚገኙ፣ ድጋፍ ለመጠየቅ የወጡ እንደተገደሉ ሪፖርቶች የደረሷቸው መሆኑንና አፍሪካዊያኑ የውጭ ዜጎች የከበደ አደጋ ላይ እንደሚገኙ እንደሚያውቁ አመልክተዋል፡፡

ማድረግ የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ እየጣሩ መሆኑንና ደኅንነታቸው የሚጠበቅበትን፣ ዕርዳታም የሚደርስበትን ሁኔታ ኮሚሽነሩ እየመከረ መሆኑን ሚስ ዊልክስ ጠቁመው አሁን ግን ሊብያዊያኑ የተሣሣተ መረጃ እንዳላቸው ማሣመን ዋናው ጉዳይ መሆኑንና በእርሱ ላይ እየሠሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"ከግብፅ ድንበር ወደ ሊብያ ዘልቀን አንድ የጎሣ መሪዎች ቡድን ቅዳሜ ዕለት አግኝተን አነጋግረናል፡፡ የስደተኞቹን ችግር፣ ከሠሃራ በስተደቡብ ካሉ ሃገሮች የመጡ ሰዎች ያሉባቸውን ስጋቶች አንስተን አስረድተናቸዋል፡፡ መረጃውን ለሕዝቡ ሊያደርሱልን፣ ሕዝባቸውን ሊያሣውቁልን ቃል ገብተውልናል፡፡" ብለዋል የዩኤንኤችሲአሯ ቃል አቀባይ ሚስ ሲቤላ ዊልክስ፡፡

በተጨማሪ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG