ዶ/ር የኔ አሰግድ ገና በልጅነት እድሜያቸው ወደ ቤልጄም በመጓዝ በውጭ ሃገር ያደጉ ኢትዮጵያዊት ምሁር ናቸው፡፡ ከ ሃያ ስምንት ዓመታት በላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማትን እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የአመራር ክህሎት ሲያሰልጥኑ ቆይተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በጋቢና ቪኦኤ ላይ እንግዳ የነበሩ ሲሆን ሶስት መጻሃፍትን ጨምሮ የተለያዩ የጥናት ጽሁፎችን አሳትመዋል፡፡ በቅርቡም 'ሊዲንግ ዊዝ ሃርት' ወይም በግርድፍ ትርጉሙ 'ከልብ መምራት' የተሰኘ አራተኛ መጽሃፋቸው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ተጽፎ ለገበያ ቀርቧል፡፡
ከልብ መመራት 'ሊዲንግ ዊዝ ሃርት'ዶ/ር የኔ አሰግድ ከዓመታት በፊት ጥናታቸውን ሲሰሩ ያነጋገሯቸው እንደ የደቡብ አፍሪካው መሪ ሲሪል ራማፎሳ፣ የቀድሞ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ኮፊ አናን፣ የቡርኪና ፋሶው መሪ እና የነጻነት ታጋይ የቶማስ ሳንካራ የቅርብ ወዳጅ እንዲሁም ሌሎች ከመሪነታቸው በላይ በሰብዓዊ ማንነታቸው የሚታወቁ መሪዎችን ባነጋገሩበት ወቅት በግላቸው ያዩትን ወይም ከጭውውቶቻቸው በመነሳት የቀሰሙትን የህይወት ክህሎት እና የአመራር ልቀት የሚያስረዳ ነው፡፡
ዶ/ር የኔ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ላይ ያሉት አብዛኞቹ ችግሮች የአመራር ክህሎት ከማጣት የመነጩ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ መጽሃፉቸውም የሃገር አመራርን ብቻ ሳይሆን የሕይወት አመራር ክህሎትን ጭምር የሚያመላክት ነው፡፡