በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የከረዩ አባ ገዳ በድብደባ መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለፁ


የከረዩ አባ ገዳ በድብደባ መገደላቸውን ነዋሪዎች ገለፁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:22 0:00

በምሥራቅ ሸዋ ዞን የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪ የኾኑ የከረዩ አባ ገዳ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተደብድበው መገደላቸውን፣ ነዋሪዎች እና የቅርብ ዘመዶቻቸው ተናገሩ። ሌሎች 18 የሚደርሱ አዛውንቶችም ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ነዋሪዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።

ስለ ድርጊቱ፣ የኢትዮጵያን መንግሥት አስተያየት ለማካተት ቢሞከርም የተገኘ ምላሽ የለም። ጉዳዩን ያውቀው እንደኾነ የተጠየቀው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ መረጃው ቢደርሰውም ማስረጃ አሰባስቦ አለማጠናቀቁን አስታውቋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ፣ የሟቹ አባ ገዳ የቅርብ ዘመድ መኾናቸውን በስልክ የገለጹ ግለሰብ፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የኾኑት የከረዩ አባ ገዳዎች አመራር አባል አቶ ጎቡ ሀዌሌ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በደረሰባቸው ድብደባ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል፡፡

እኚኹ አስተያየት ሰጪ መንሥኤውን በግልጽ ባልጠቀሱት የኀይል ድርጊት፣ ወደ 18 የሚኾኑ አዛውንቶች መደብደባቸውን ገልጸው፣ በአባ ገዳ ጎቡ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን ከባድ ስለነበር ለኅልፈት መዳረጋቸውን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ሟቹ ጎቡ ሀዌሌ፣ በገዳ ሥርዐት ስያሜ፣ “አባ ሰበታ” በመባል ነበር የሚታወቁት፡፡ ይኸውም፣ “አባ ቦኩ” በሌለበት የገዳ ሥርዓትን የሚመራ ማለት መኾኑን አስተያየት ሰጪው አስረድተዋል።

በዕለቱ ለድብደባ እና ግድያ የሚያበቃ የጸጥታ ችግር በአካባቢው እንዳልነበር የፈንታሌ ወረዳ ነዋሪው አውስተዋል፡፡ ነገር ግን ከኹለት ቀናት በፊት፣ በቦሰት እና በመርቲ ወረዳዎች አዋሳኝ በኾነው ቦሌ በሚባል ቦታ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ በሚነገረው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል ግጭት እንደነበር ተናግረዋል።

“ከኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ጋራ ግጭቱ የተፈጠረበት ቦታ፣ አሁን ጥቃት ከተፈጸመበት ቦታ ይርቃል። ያ ኹኔታ ከተከሠተ ከኹለት ቀናት በኋላ ነው፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወደ አባ ገዳዎች ቀዬ የመጡት፤” ሲሉ ያስረዱት ነዋሪው፣ ሕይወታቸው ካለፈው አባ ገዳ ጎቡ ሀዌሌ በተጨማሪ፣ አቶ ቦሩ ጅሎ የሚባሉት የአባ ገዳዎች አባል፣ በድብደባው ክፉኛ መጎዳታቸውንና በወለንጪቲ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንዳለ ገልጸዋል።የተቀሩት ተጎጂ አረጋውያን፣ ያለሕክምና በዚያው በመኖሪያቸው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ መሣሪያ አንግቶ ወደማይገባበት የአባ ገዳዎች ቀዬ ገብተው ጥቃቱን እንደፈጸሙባቸው ገልጸዋል። በጉዳዩ ላይ ምላሽ ለማግኘት ከፈንታሌ ወረዳ ፣ ከምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር፣ ከኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት፣ ከኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና ከኦሮሚያ ጸጥታ እና ደኅንነት ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ መረጃው ቢደርሰውም ማስረጃ አሰባስቦ አለማጠናቀቁን አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG