በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኬንያ አምራቾች የአገሪቱን ገበያ ባጥለቀለቁት የቻይና ገቢ ምርቶች ብርቱ ተቃውሞ አነሡ


ናይሮቢ፣ ኬንያ
ናይሮቢ፣ ኬንያ

የኬንያ የስታቲስቲክስ ቢሮ እንዳስታወቀው፣ ቻይና፣ ከ20 በመቶ በላይ የሚኾነውን የገቢ ንግድ ወደ አገሪቱ በማስገባት ግንባር ቀደም ናት።

ብዙ የሀገር ውስጥ አምራቾች፥ ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች ብዛት፣ ዋና ገቢያቸውን እየጎዱ እንደኾነ ይናገራሉ።

በናይሮቢ የሚገኘው የካሙኩንጂ ገበያ፣ ከቻይና በገቡ ሸቀጦች የተሞላ ነው። ክሪስቲንንጄሪ፣ በዚኽ ገበያ ውስጥ ነጋዴ ሲኾኑ፣ የናይሮቢ አስመጪ ነጋዴዎች ማኅበር ባለሥልጣን ናቸው። የቻይና ምርቶችን በጣም የሚያንቀሳቅሳቸው፣ የዋጋቸው ዝቅተኛነት እንደኾነ፣ ንጄሪ ያስረዳሉ፡፡

“ከቻይና የመጡትንና የሀገር ውስጥ ምርቶችን ዋጋ ስታወዳድሩ፣ ከቻይና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች ርካሽ ናቸው፤” የሚሉት ንጄሪ፣ “እኔ እንደ ነጋዴ ሸጬ የተወሰነ ትርፍ ማግኘት እንድችል፣ ርካሹ ዋጋ ያለው የት ነው ብዬ አፈላልጋለኹ፤” ሲሉ ችግሩን ያመለክታሉ፡፡

የንጄሪ ደንበኛ ሙሴ ዋቺራ፣ “የኬንያ ምርቶች ለእኛ እጅግ ውድ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ አማራጭ ሳይኖረን ሲቀር እንገዛቸዋለን፤ ነገር ግን በጣም ውድ ስለኾኑ፣ የቻይናን ምርቶች እንመርጣለን፤” ሲል፣ ንጄሪ የተናገሩትን ያረጋግጣሉ፡፡

በዚኽ ዓመት መግቢያ ላይ፣ አነስተኛ ነጋዴዎች፣ የቻይና ምርቶችን ከሚያስመጡ ተፎካካሪዎቻቸው ጋራ፣ ፍትሐዊ ያልኾነ ውድድር መኖሩን በመግለጽ፣ ተቃውሟቸውን በሰላማዊ ሰልፍ አሰምተዋል፡፡

ንጄሪ፣ የቻይና ነጋዴዎች ወደ እነርሱ ገበያ ወርደው እየገቡ እንደኾነ ጠቅሰው፣ “አምራቾቹ ከቻይና መጥተው ምርቶቻቸውን እዚኽ ኬንያ ውስጥ መሸጥ ከጀመሩ፣ እኛ ኬንያውያን ነጋዴዎች፣ ከገበያው ተገፍተን እንወጣለን፤” ሲሉ ያላቸውን ስጋት ጠቁመዋል፡፡

ከኬንያ የገቢ ምርቶች፣ 20ነጥብ5 በመቶ ድርሻ ያላት ቻይና፣ ብቸኛዋ ግንባር ቀደም ኾና መቀጠሏን፣ የአገሪቱ የስታስቲክስ ቢሮ አመልክቷል።

የኬንያ አምራቾች እንደሚናገሩት፣ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ከውጭ የሚገቡ ምርቶች፣ የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን እየተፈታተኑ ነው።

መንግሥት የማምረት ወጪን ለመቀነስ፣ የግብር ቅነሳን ጨምሮ የንግዶቻቸውን መሳለጥ የሚጠብቅ ርምጃዎችን እንዲወስድ፣ አምራቾቹ ይፈልጋሉ።

የኬንያ አምራቾች ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንተኒ ምዋንጊ፣ “እኛ በምናደርገው ነገር ጣልቃ የሚገቡ ብዙ ተቆጣጣሪ ኤጄንሲዎች እና የመንግሥት ተቋማት አሉ፡፡ በመካከላቸው ቅንጅት ያለ መኾኑን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

አያይዘውም፣ “መደራረብ አለመኖሩን የምናረጋግጠው እንዴት ነው? ፓርላማው እና እየወጡ ያሉ ሕጎች እና ፖሊሲዎች፣ ምርትን ለማሳደግ እንጂ የገቢ ምርቶችንና ፍጆታዎችን ለማበረታት እንዳልኾነ እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?” ሲሉም አክለው ይጠይቃሉ፡፡

በኬንያ ገበያ፣ መናኛ እና ርካሽ የቻይና ምርቶች ጥራት ላይ ብዙ ጥያቄዎች ሲነሡ ቆይተዋል።

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ፣ ርካሽ የቻይና ምርቶች ቢተረፈረፉም፣ በሚቀጥሉት 25 ዓመታት፣ አፍሪካ በሁሉም ዓይነት የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች ግንባር ቀደም ትኾናለች፤ ይላሉ ምዋንጊ። ያን ጊዜ፣ “አፍሪካ ትልቁ የሰው ኀይል ይኖራታል፤” የሚሉት ምንዋጊ፣ “አፍሪካ በሐሩር ክልል ውስጥ ስለኾነች፣ የፀሐይ ኃይል ለማግኘት ዕድሉ አለን፡፡

አፍሪካ፣ ከኮንጎ ወንዝ እና ከመሳሰሉት የታዳሽ ኃይል ምንጮች አሏት፡፡ አፍሪካ 50 ከመቶ የሚታረስ መሬት ይኖራታል፡፡ ስለዚህ መጻኢው ጊዜ፣ አፍሪካው ውስጥ ነው፤” ሲሉ፣ አህጉሪቱ አላት ያሉትን ተስፋ ዘርዝረዋል፡፡

ይኹን እንጂ ምዋንጊ፣ የአፍሪካ ሀገራት፣ እንደ ቻይና ካሉ ዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋራ ለመወዳደር እና የዓለም አምራቾች(የማኑፋክቸሪንግ) ማዕከል እንዲኾኑ፣ የማምረቻ ቦታቸውን ማዘመንና ማሻሻል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG