· የኬንያ መንግሥት፥ 750ሺሕ ሠራተኞችን ለመላክ ከ10 ሀገራት ጋራ ስምምነት አድርጓል
የኬንያ መንግሥት፥ ወደ ካናዳ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ እና አንዳንድ የባሕረ ሠላጤ ሀገራት፣ ሠራተኞችን ለመላክ፣ ከየሀገራቱ ጋራ ስምምነት ላይ መደረሱንና ለመድረስ ማቀዱን አስታውቋል። ስምምነቱ፣ ኬንያውያን፥ በውጪ ሀገራት ሥራ እንዲያገኙ፣ ጥርጊያ መንገድ ይከፍትላቸዋል፤ ተብሏል።
የሠራተኛ መብት ተቆርቋሪዎች እንደሚሉት ግን፣ እንዲህ ዐይነቱ ስምምነት፥ በተለይም በባሕረ ሠላጤው ሀገራት፣ ሠራተኞችን ለብዝበዛ እና ጥቃት ያጋልጣል።
በግምት ወደ 750 ሺሕ የሚጠጉና በአገር ውስጥ ሥራ ማግኘት ያልቻሉ ዜጎች፣ በውጪ ሀገራት ሥራ እንደሚያገኙ፣ ኬንያ ተስፋ ታደርጋለች፡፡
መንግሥት እንደሚለው፣ የባሕረ ሠላጤ ሀገራትን ጨምሮ ለ10 ሀገራት ሠራተኞችን ለመላክ፣ ስምምነት ላይ ተደርሷል። ይህም፣ ሥራ ዐጥነት የፈጠረውን ጫና ያቃልላል፤ ተብሏል፡፡
ጀፈሪ ካይቱኮ፣ የሠራተኛ ጉዳይ ሚኒስትር ፣ “ሰዎች የማያቋርጥ እንቅስቃሴ ላይ ናቸው። በመኾኑም፣ የኬንያ መንግሥት፣ ለአገሩ ሠራተኞች ተዘዋውሮ መሥራት ቅድሚያ ሰጥቷል። ለዚያም ነው፣ የባሕረ ሠላጤ ሀገራትን ጨምሮ ከተወሰኑ አገሮች ጋራ፣ የሥራ ስምምነት የተፈራረምነው። ለሌሎች በርካታ ሀገራትም፣ ስምምነቱን እንዲፈጽሙ ሐሳብ አቅርበናል፤” ብለዋል።
ሰሲሊያ ዋንጂኩ፣ ወደ ባሕረ ሠላጤ ሀገራት ከሚሔዱት 170 ሺሕ ሠራተኞች አንዷ ናት፡፡ ግማሽ የሚኾኑቱ፣ በቤት ሠራተኝነት እንደሚሠማሩ መንግሥት አመልክቷል።
“ኬንያ ውስጥ ጥሩ ሥራ ስለማላገኝ፣ ራቅ ወዳለው ሳዑዲ አረቢያ ለመሔድ ወሰንኹ። ለራሴ እና ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችለኝን ሥራ ለማግኘት እንድችል ነው ለመሔድ የተስማማኹት፡፡”
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት፣ ኬንያ፥ በውጪ የሚገኙ ዜጎቿ ከሚልኩት የውጪ ምንዛሬ፣ አራት ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች። በዐዲሱ ስምምነት፣ ይህን ገቢዋን፣ በእጥፍ ለማሳደግ ዐቅዳለች፡፡
የመብት ተቆርቋሪዎች ግን፣ ዜጎች፣ ሥራ ለማግኘት ሲሉ በሚያደርጉት ጥረት መሀል፣ በውጪ ሀገራት ባሉ ቀጣሪዎቻቸው ጥቃት ይደርስባቸዋል፤ ሲሉ ይናገራሉ። የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴሩ እንደሚለው፣ እ.አ.አ በ2021፣ 41 ኬንያውያን፣ በሳዑዲ አረቢያ በመሥራት ላይ ሳሉ ሕይወታቸው አልፏል። በኬንያ ያሉ ሥራ አፈላላጊ ድርጅቶች፣ የሠራተኞችን ብዝበዛ እና ጥቃት ለማስቆም፣ በቂ ጥረት እያደረጉ አለመኾናቸውን፣ አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።
ፒስ ሙቴዉ፣ የአንድ ሥራ አፈላላጊ ድርጅት ሓላፊ ሲኾኑ፣ ወደ ውጪ የላኳቸው አንዳንድ ወጣት ሴቶች፣ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ይናገራሉ።
“ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ ለ26 ሴቶች መብት ቆሜያለኹ። 10 የሚኾኑቱ፣ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል። 16ቱ ደግሞ ቀጣሪያቸውን ቀይረዋል። ይህን በማድረጌ ግን ችግር ገጥሞኛል።” ፒስ ሙቴዉ እንደሚሉት፣ ያን በማድረጋቸው፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት፣ ሠራተኛ ከመላክ አግደዋቸዋል።
ፌይዝ ሺሚላ፣ በሳዑዲ አረቢያ፣ ለአንድ ዓመት ተኩል ሠርታ ተመልሳለች፡፡ ጥቃት ደርሶባት እንደነበርና የሥራ ኹኔታው እጅግ ከባድ እንደነበር ትናገራለች፡፡
“ከ18 እስከ 19 ሰዓታት እሠራ ነበር። መድኃኒት የለም፤ የዕረፍት ሰዓት የለም፤ ዕረፍት መውጣት የለም፤ ለአፍታ እንኳን የሚያስፈልግኽን ትንሽ ዕረፍት አታገኝም። ትርፍራፊ ምግብ ነበር የሚሰጡኝ። መኝታውም የማይመች ቦታ ነበር። ለበርካታ ጊዜያት በቀጣሪዬ ተደፍሬያለኹ። ለምን ያህል ጊዜ እንደኾነ መቁጠር አልችልም።”
የሕግ ባለሞያው ጃን ሙሪሪ፣ ለፌይዝ እና 12 ለሚኾኑ ሌሎች ሠራተኞች ጥብቅና ቆመዋል። “መንግሥት ከጥቃት አልጠበቀንም፤” በሚል ሠራተኞቹ ክሥ አቅርበዋል። ሠራተኞቹ፣ ጥቃት በሚፈጸምባቸው ወቅት፣ መንግሥት እንዲደርስላቸው አቤቱታ እንደሚያሰሙ የሚገልጹት ሙረሪ፣ “መንግሥት ግን፣ ምንም ዐይነት ርዳታ አይሰጥም፤” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
ጃን ሙሪሪ የሚገኙበት የሕግ ቡድን፥ ሠራተኞች ደኅንነታቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ፣ ወደ ባሕረ ሠላጤ ሀገራት እንዳይሔዱ፣ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲያስተላልፍ ጠይቀዋል።
ከባሕረ ሠላጤው ሀገራት ጋራ የተደረሰው ስምምነት፣ ሠራተኞችን ከጥቃት ይጠብቃል፤ ሲል መንግሥት ይናገራል። ነቃፊዎች ግን ጥርጣሬ አላቸው።