ኬንያ ውስጥ እጅግ የናረው የነዳጅ ዋጋ የሰዉን ህይወት በእጅጉ ማክበዱን የፈረንሣይ የዜና ወኪል ከናይሮቢ ዘገበ።
የኢነርጂና የተፈጥሮ ዘይት ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ዛሬ ያወጣው “ከፍተኛ” የተባለ ጭማሪ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋን አንድ የአሜሪካ ዶላይ ከ36 ሣንቲም ወይም ከ200 የኬንያ ሽልንግ በላይ እንዲያሻቅብ የደረገው መሆኑ ተገልጿል። (በዛሬ ምንዛሪ የኢትዮጵያ 75 ብር ከ03 ሣንቲም መሆኑ ነው)
ኬንያዊያን እንዲሁም አልቀመስ ባለው የምግብ ዋጋ፣ በአዳዲስ ግብሮችና ቀረጦች እንዲሁም በሽልንግ የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል እየተሰቃዩ መሆናቸው እየተነገረ ነው።
ሚኒስትሩ ዴቪስ ቺርቺር ለፓርላማው የኢነርጂ ጉዳዮች ኮሚቴ ማብራሪያ ሲሰጡ ለዋጋው ማሻቀብ ምክንያት የሆነው አውራዎቹ ዘይት አውጭና ላኪዎች ሳዑዲ አረቢያና ሩሲያ ነኀሴ መጨረሻ ላይ በቀደሙት አሥር ወራት ታይቶ በማይታወቅ መጠን ዋጋቸውን ማናራቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የኬንያ የገንዘብ ግሽበት መጠን ባለፈው ወር ወደ 6.7 ከመቶ ዝቅ ያለ ቢሆንም የቤንዚን ዋጋ በ22 ከመቶ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋጋ በ 50 ከመቶ፣ ስኳር በ61 ከመቶ ባቄላን የመሳሰሉ የለት ተለት ፍጆታዎች ደግሞ በ30 ከመቶ ማሻቀባቸው ተገልጿል።
ናይሮቢ ውስጥ የናፍጣ ዋጋ 201 ሽልንግ ወይም 75 ብር ከ53፣ የላምባ ዋጋ ደግሞ 202 ሽልንግ ከ61 ወይም 76 ብር ከ14 ሣንቲም ደርሷል።
መድረክ / ፎረም