ኢትዮጵያን በሚያዋስነው የኬንያ ድንበር በግጦሽ መሬትና ከብቶችን ዝርፎ በመንዳት በተቀሰቀሰ ግጭት ከ20 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ ወደ 50 የሚጠጉ የደረሱበት አይታወቅም።
በኬንያ ፖሊስና የምገናኛ ብዙሃን ይፋ የሆኑ መረጃዎች እንደሚያትቱት ጥቃቱ የደረሰው በኬንያዊያኑ ላይ ነው።
የሮይተርስ የዜና ምንጭ የስምጥ ሸለቆ ክፍለሃገር የፖሊስ አዛዥ ኦስማን ዋርፋን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በጥቃቱ 19 ኬንያዊያን ተገድለዋል።
ቆይተው የወጡ ዘገባዎች የሟቾቹን ቁጥር ከ20 በላይ ሲያደርሱ፣ ጉዳት ከደረሰባቸውም ሴቶችና ህጻናት ይገኙባቸዋል።
ሰኞለት ከኢትዮጵያ ድንበር ጨው ባህር አካባቢ ገስግሰው የመጡ አርብቶ አደሮች ቶንዶያንግ በሚባለው የቱርካና ሃይቅ አካባቢ መንደር ደርሰው፤ በኬንያዊያኑ ላይ ተኩስ በመክፈት እንደገደሏቸውና ከብቶቻቸውን እንደነዱ የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል።
አንዳንድ የአይን ምስክሮች ከኢትዮጵያዊያኑም የተገድሉ እንዳሉና በጠቅላላው የግጭቱ ተጎጂዎች ቁጥር ከ42 በላይ እንደሆነ ተናግረዋል። በጥቃቱ ከተገደሉት በእድሜ ትንሹ የ3ዓመት ወንድ ልጅ ሲሆን፤ የመንደሩ ነዋሪዎች ያለምንም ማማረጥ በጥይት እንደተደበደቡ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በኩል በጉዳዩ ላይ የተሰጠ መግለጫ የለም። የጎሳዎች በግጦሽ መሬትና በከብት መንዳት ግጭት መጠመድ በአካባቢው የተለመደ ክስተት ነው።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ የአደጋ መከላከልና የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት በደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ጨምሯል ሲል ማስታወቁ አይዘነጋም።
የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ በጥር ወር መጀመሪያ 2.8 ሚሊዮን ዜጎች የውጭ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አስታውቆ፤ ተገቢው እርዳታም እንዲደረግለት ለጋሾችን ጠይቆ ነበር። ለቪኦኤ በስልክ ቃላቸውን የሰጡት የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ታደሰ በቀለ፤ የተረጂዎቹ ቁጥር 3.2 ሚሊዮን እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎ የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ባወጣው መረጃ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ በዝናብ እጥረት ሳቢያ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ድርቅ በመከሰቱ የግጦሽ መሬት ሲመናመን አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው ግጦሽ ፍለጋ ወደ ግጭት ያመራሉ የሚል ስጋት እንዳደረበት አስታውቆ ነበር።
በአዲስ አበባ የWFፒ ቃል-አቀባይ ሱዛና ኒኮል ውሃና የከብት መኖ ለማጓጓዝ ጥረት ቢደረግም፤ ከችግሩ ስፋት አንጻር፤ ሁሉን ለማዳረስ አለመቻሉንና የከብቶች ሞት መቀጠሉን በወቅቱ ገልጸው ነበር።
“የከብት መኖና የውሃ እጥረት በአንዳንድ አካባቢዎች በእጅጉ የጠና ሆኗል። ከብቶቹ መሞታቸው ከቀጠለ፤ ችግሩ ይባባስና የሁሉንም ሰው ደጅ ያንኳጓል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ እጥረት የተከሰተው በዚህ ወር መግቢያ የአለም ባንክ በአለም ዙሪያ የ36 ከመቶ የምግብ ዋጋ ጭማሪ በዚህ አመት እንደተስተዋለ ይፋ ባደረገበት ማግስት ነው።