በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን “መስቀለኛ መንገድ” ላይ ነው


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ መንገድ ላይ ለሽያጭ የተሰናዱ ጋዜጦች እአአ ሰኔ 24/ 2019
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ መንገድ ላይ ለሽያጭ የተሰናዱ ጋዜጦች እአአ ሰኔ 24/ 2019

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ነው ነፃ ሚዲያ በሃገሪቱ የሚሰራበት አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚያደርጉ ቃል የገቡት። ይሁንና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 በፌዴራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት መቀሰቀስቀሱን ተከትሎ በተፈጠሩ ሁኔታዎች በርካታ ጋዜጠኞች ማስፈራራት፣ እስር እና ከሃገር የመባረር ዕጣ ጭምር እንደገጠማቸው ይናገራሉ። ሄንሪ ዊልኪንስ ከወልድያ ባጠናቀረው ዘገባ ተመልክቶታል።

የፕሬስ ነፃነት እንዲጎለብት የሚታገለው እና ዋና መቀመጫውን በፓሪስ ያደረገው ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን፣ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከአራት ዓመት በፊት ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ኢትዮጵያን በዓመታዊው የአገራት የፕሬስ ነፃነት አያያዝ ሰንጠረዥ አርባ ደረጃዎች ከፍ አደረጋት።

አስርታት ላስቆጠረ በመንግሥት ለሚፈጸም የሚዲያ አፈና እና ጭቆና ይህ ከታላቅ እመርታ የሚቆጠር ነው። ነገር ግን በመንግሥት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ወዲህ ታዲያ የኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት አያያዝ ደረጃ ዳግም ማሽቆል ያዘ።

የዘንድሮውን የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ለማሰብ በተሰናዳው በዚህ ዘገባ የአሜሪካ ድምፅ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ሥራቸውን ለመስራት የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች እንዲያስረዱ ጠይቋል። ለአሶሼትድ ፕሬስ ይሰራ የነበረው ኤልያስ መሰረት ለአሜሪካ ድምፅ በሰጠው አስተያየት የፕሬስ ነፃነት በኢትዮጵያ፣

“መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለው” ይላል።

“በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ሞያው የሚጠይቀውን ክህሎት አሟልቶ እና መርሆውን ተክትሎ የመስራት ብቃት ማነስ እና ጽንፈኝነት" የመገናኛ ብዙኃኑ 'ዓይነተኛ መገለጫዎች ሆነዋል' ማለት እችላለሁ። ይህ ሁኔታ እንዲለወጥ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሥራቸውን በነፃነት እንዲሠሩ የመፍቀድ ኃላፊነት ያለበት ይመስለኛል። ይህም ማለት ያለ ምንም ትንኮሳ እና ማስፈራራት ማለት ነው።” ብሏል።

አሰግድ ሙሉጌታ የመንግሥታዊው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባልደረባ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአጠቃላይ የፕሬስ ነፃነት መሻሻል አሳይቷል የሚል አስተያየት አለው። እእአ በ2018 ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችን ከእስር ለቀቁ። ሆኖም ኢትዮጵያን ዋነኝዋ የጋዜጠኞች አሳሪ አገር ያደረጋትን እና 46 ጋዜጠኞች የታሰሩበትን 2021ዓም የጠቀሱት ጋዜጠኞች፣

“ያ ቀደም ሲል ተመዝግቦ የነበረው እመርታ ተቀልብሷል” ባይ ናቸው።

በመንግሥት የሚደገፈው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ትናንት ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ ባለፈው እሁድ የሲቪል ልብስ በለበሱ ሰዎች ተይዞ ከተወሰደ በኋላ የተወሰደበት ያልታወቀውን ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

አሚር አማን ኪያሮ
አሚር አማን ኪያሮ

አሚር አማን ኪያሮ እና ባልደረባው ቶማስ እንግዳ የተባሉ ሌሎች ሁለት ጋዜጠኞችም በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ባለፈው ህዳር ወር ተይዘው በቅርቡ በመጋቢት ወር ነው ከእስር የተለቀቁት። ይሁንና በጦርነቱ ወቅት ተደንግጎ የነበረውን እና የተከሰሱባቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እና የጸረ-ሽብር ህግ ተላልፈው መገኘታቸው በፍርድ ቤት ከተረጋገጠ ገና ሌላ ተጨማሪ የእስራት ጊዜ ሊጠብቃቸው ይችላል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2018ዓም በፊት በነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት አስተዳደር ህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ - ህወሓት የአገሪቱን የፖለቲካ ሥርዓት በበላይነት ይመራ እንደ ነበር ያስታወሰው የራዲዮ ጋዜጠኛው አሰግድ በበኩሉ “አሁንም መሻሻል አለ” ይላል።

"ማነቆዎች የበዙበት አሰራር፣ የበዛ ሳንሱር እና ጋዜጠኞች ላይ የሚፈፀም ድብደባ፣ ብዙ-ብዙ ጫናዎች ነበሩ። አሁን አሁን የዩቲዩብ እና የኢንተርኔት ሚዲያዎች መበራከት እያየን ነው። ይህ መልካም ነገር ነው።”

ሲሳይ ሳህሉ የሪፖርተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነው።

“የግሉ ፕሬስ ባብዛኛው የመንግሥት ባለሥልጣናትን ምላሽ ማግኘት አይቻላቸውም” ይላል።

"የእኔ እና የጓደኞቼ ልምድ በህዝብ መገናኛ ብዙኃን ከሚያገለሉ ጋዜጠኞች ልምድ ፍጹም የተለየ ነው። እንደ አንድ የግል ጋዜጣ ሰራተኛ ለእኔ መረጃ ማግኘት በእጅጉ አዳጋች ነው። ለአንድ ቀላል ዘገባ አስር ባለስልጣን ጋር መደወል ሊኖርብኝ ይችላል።

ሲሳይ አክሎም “አስር የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋ ደውለህ ራሱ የመንግሥትን እንቅስቃሴዎችን ወይ መንግሥት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች አስመልክቶ ለምታቀርበው ጥያቄ መልስ መስጠት ላይፈቅዱ ይችላሉ።” ብሏል።

"(ስልክ) ደውለህ ስትጠይቃቸው የሚሰጡህ ፍንጭ የለም። ደብዳቤ እንጽፋለን። መልስ የለም። በመጨረሻው ዘገባውን ለንባብ በምናበቃበት ወቅት ግን (በቀጥታ) ከቢሯችን ይመጣሉ። አንዳንዴም ስልክ ደውለው የቃላት ጦርነት ይጀምራሉ .. ይህም መረጃ ሰጥተውን ወይም ሳይሰጡን ሊሆን ይችላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለተነሱት ጥያቄዎች የኢትዮጵያን መንግሥት ምላሽ ለማካተት የመንግሥቱ ቃለ አቀባይ ለጊዜው አልተገኙም። የዘንድሮው የዓለም ፕሬስ የአገራት መለኪያ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያን ባለፈው ዓመት ከነበረችበት 13 ደረጃዎች ዝቅ አድርጎ 114ተኛ ላይ አስቀምጧታል።

XS
SM
MD
LG