በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አይቮሪ ኮስት የፈረንሳይ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ ጠየቀች


የአይቮሪ ኮስት ወታደሮች ልምምድ እያደረጉ ሉምቢላ ካምፕ፣ ዣክቪል፣ አይቮሪ ኮስት፣ እ አ አ የካቲት 16 2022
የአይቮሪ ኮስት ወታደሮች ልምምድ እያደረጉ ሉምቢላ ካምፕ፣ ዣክቪል፣ አይቮሪ ኮስት፣ እ አ አ የካቲት 16 2022

አይቮሪ ኮስት ትላንት ማክሰኞ ለዐስርት ዓመታት በሀገሯ የቆዩ የፈረንሳይ ወታደሮች ሀገሯን ለቀው እንዲወጡ በመጠየቅ ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ጋራ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጡ የአፍሪካ ሀገራትን ተቀላቅላለች።

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አልሳን ኦታራ እንዳስታወቁት በአይቮሪ ኮስት የነበሩት 600 ወታደሮች ከጥር ወር ጀምረው ከሀገራቸው መውጣት ይጀምራሉ።

"በአይቮሪ ኮስት የሚገኙ የፈረንሳይ ወታደሮች በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ እንዲወጡ ወስነናል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በአሁኑ ወቅት በፈረንሳይ ጦር የሚተዳደረው የፖርቱ ቡዌት አንድ ሻለቃ ወታደራዊ ክንፍ ለአይፎሪያን ጦር እንዲተላለፍ መወሰኑን ጨምረው አመልክተዋል።

ይህ የኦታራ ውሳኔ የመጣው ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትም በተመሳሳይ ሁኔታ የፈረንሳይ ጦር ሀገራቸውን ለቀው እንዲወጡ እየጠየቁ ባሉበት ወቅት ነው።

ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀርን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ፈረንሳይ ሀገራቸውን ለቃ እንድተወጣ ያደረጉ ሲሆን፣ በቅርቡም ሴኔጋል እና ቻድ ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል። በተለይ ቻድ በአፍሪካ በጣም የተረጋጋች እና ታማኝ የፈረንሳይ አጋር ሆና የኖረች ሀገር ስትሆን፣ ርምጃው ቀጠናው ከፓሪስ ጋራ ያለው ግንኙነት ከፍተኛ መዋቅራዊ ለውጥ እያደረገ መሆኑን እንደሚያሳይ ተንታኞች ያመለክታሉ።

የቅኝ አገዛዝ ከፈረሰ ወዲህ፣ ፈረንሳይ ወታደሮቿን ካሰፈረችባቸው የአፍሪካ ሀገራት፣ 70 በመቶ ከሚሆኑት እንድትወጣ ተደርጋለች። በአሁኑ ሰዓትም በጅቡቲ የሚገኙት 1ሺሕ 500 ወታደሮቿ እና በጋቦን የሚገኙት 350 ወታደሮቿ ብቻ በአፍሪካ ቀርተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG