በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሰላም ሥምምነቱ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ተናገሩ


በሰላም ሥምምነቱ ላይ ተቃውሞ እንደሌላቸው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:32 0:00

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት እንዲያበቃ በህወሃት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በቅንነት እና ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ከተተገበረ፣ ኤርትራ ምንም ተቃውሞ እንደሌላት የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትናንት ለሀገራቸው የመንግሥት ሚዲያዎች በሰጡት ቃለምልልስ ገለፁ።

ኤርትራ ወደ ትግራይ ጦርነት የገባችው ተገዳ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ "ሁኔታው ጥንቃቄ በተሞላበት ክትትል ሊረጋገጥ ይገባል" ብለዋል።

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትናንት ከሀገራቸው መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት አንድ ሰዓት ከሀያ ደቂቃ የፈጀ የመጀመሪያ ክፍል ቃለምልልስ፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተደረገው ጦርነት ኤርትራ ተሳትፎ እንደነበራት በይፋ የገለፁት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ጦርነቱን ለማስቆም በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ሥምምነት በቅንነት እና ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ከተተገበረ ኤርትራ ምንም ተቃውሞ እንደማይኖራት እና ሁኔታውን ግን በጥንቃቄ እንደምትከታተለው ያመለከቱት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፣ ህወሃት የጦርነት ማቆም ስምምነቱን የፈረመው ወታደራዊ ሽንፈቱን ለመሸፈን ነው" ሲሉ ተችተዋል።

"ጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ህይወት የቀጠፈ ነው" ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጦርነቱን የቀሰቀሱ እና ያባባሱ ኃይሎች ተጠያቂነት ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ ይሄንን ቃለ መጠይቅ ከሰጡ በኃላ ከህወሃት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የኤርትራ ኃይሎች ትግራይ ክልል ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በጋራ ባካሄዱት ምርመራ ይፋ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ ከሰላም ሥምምነቱም በኃላ የኤርትራ ኃይሎች በትግራይ መቆየታቸው እና የሰብዓዊ ጥሰት ማድረስ መቀጠላቸው ሲዘገብ ቆይቷል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ግን በዚህ ዙሪያ አስተያየት አልሰጡም።

ህወሃት ከሥልጣን ሲወርድ፣ እ.አ.አ በ2018 በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ከፍተኛ ተስፋ አጭሮ እንደነበር በቃለምልልሳቸው ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ይህ ሁኔታ ዋሽንግተንን ደስ ባለማሰኘቱ ህወሃት ወታደራዊ ጥቃት እንድትፈፅም ገፋፍተዋል በማለት አሜሪካን ከሰዋል። "በኃይል ሚዛኑ ላይ የነበረው የተሳሳተ ስሌት" ሲሉ የገለፁት ሁኔታም ለአስከፊ እልቂት መዳረጉን አስረድተዋል።

በዚሁ ቃለምልልስ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አዲሱን አሜሪካ ለዓለም አቀፍ እና ቀጠናዊ ሰላም የነደፈችውን ብሔራዊ የደህንነት ስትራቴጂ 'የአንድ ሀገር የበላይነት የሚያስጠብቅ የዓለም ስርዓትን ለማጠናከር የወጣ ነው' ሲሉ ነቅፈዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ ለሰማንያ ዓመታት ያክል በኤርትራ ላይ ያደረሰችውን ታሪካዊ በደል የሚያጎላ ደብዳቤ መንግስታቸው ለትራምፕ አስተዳደር መፃፉን አስታውሰው፣ ይህ ጥረታቸው ግን ምንም ዓይነት የጎላ የፖሊሲ ለውጥ እንዳላስከተለ አመልክተዋል።

በዚህ ዙሪያ ከዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስካሁን የተሰጠ ምላሽ የለም።

XS
SM
MD
LG