የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር፣ "እስራኤል ካትዝ ሃገራቸው ከሃማስ ጋራ የምታካሂደውን ጦርነት ካጠናቀቀች በኋላም የአካባቢውን ደኅንነት ትቆጣጠራለች" ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሚንስትሩ ዛሬ ማክሰኞ በX ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባወጡት ጹሑፍ "የሃማስን ወታደራዊ እና የመንግሥት አቅም ካስወገደች በኋላ እስራኤል ጋዛ ላይ የፀጥታ ቁጥጥር ለማድረግ ሙሉ በሙሉ የመንቀሳቀስ ነፃነት ታገኛለች" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ጋዛን በሚመለከት ያላቸውን ሐሳብ በዌስት ባንክ ይዞታዎቿ ወታደሮቿ የሽብርተኞችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ከሚያደርጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋራ አመሳስለውታል፡፡
ይህ የእስራኤል ጋዛን የመቆጣጠር ፍላጎት ግን ከጦርነት በኋላ ሊኖር በሚገባው ሁኔታ ላይ አሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች ካላቸው ምልከታ ጋራ ይጻረራል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በጥቅምት ወር ሲናገሩ የጋዛ ጦርነት መቆም "ሀማስ እንደሚወጣ እስራኤልም እንደማትቆይ በሚያረጋግጥ መንገድ" መኾን እንዳለበት አሳስበዋል፡
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ በበኩላቸው ድርጅታቸው አንዳንድ የዌስት ባንክን አካባቢዎች የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር ጋዛንም ይቆጣጠራል ብለው እንደሚገምት ባለፈው መስከረም ተናግረዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የጋዛ የጤና ኃላፊዎች እስራኤል ዛሬ ባደረሰችው ጥቃት ዐስር ሰዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል፡፡ የእስራኤል ጦር በበኩሉ በደቡባዊ ጋዛ ባካሄደው ወታደራዊ ጥቃት ላይ ሁለት ወታደሮቹ መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
መድረክ / ፎረም