በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምድር ላይ ማጥቃት ማካሔዷን አስታወቀች


በእስራኤል ጦር የተለቀቀው ምስል በሰሜናዊ ጋዛ በታንክ እና እግረኛ ጦር “ያነጣጠረ ጥቃት” ያሳያል፤ እአአ ጥቅምት 26/2023
በእስራኤል ጦር የተለቀቀው ምስል በሰሜናዊ ጋዛ በታንክ እና እግረኛ ጦር “ያነጣጠረ ጥቃት” ያሳያል፤ እአአ ጥቅምት 26/2023

የእስራኤል ጦር፣ ዛሬ ኀሙስ፣ በጋዛ ሰርጥ የምድር ላይ ጥቃት ወረራ ማካሔዱን አስታውቋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ ታንኮች እና የእግረኛ ወታደሮች ወደ እስራኤል ግዛት ከመመለሳቸው በፊት፣ በርካታ የአሸባሪ ሕዋሶችን፣ መሠረተ ልማቶችንና የፀረ ታንክ ሚሳኤል ማስወንጨፊያ ቦታዎችን እንደ ደበደበ ጦሩ ገልጿል፡፡

ሠራዊቱ በመግለጫው፣ ይህ ለ“ቀጣይ የውጊያ ዘመቻዎች” የዝግጅት ርምጃ እንደኾነ ጠቁሟል፡፡

እአአ በጥቅምት ሰባቱ የመጀመሪያው የሐማስ ጥቃት፣ 1ሺሕ400 የሚደርሱ ሰዎች በእስራኤል ውስጥ እንደሞቱ የሚታወስ ሲኾን፣ አብዛኛዎቹ ሲቪሎች ነበሩ።

በሌላ በኩል፣ የፍልስጥኤም ጤና ሚኒስቴር፣ በጋዛ ቢያንስ 6ሺሕ546 ሰዎች እንደተገደሉና የሚበዙት ሟቾችም ሴቶች እና ሕፃናት እንደኾኑ አስታውቋል።

የአሜሪካ እና የእስራኤል ባለሥልጣናት፣ በሐማስ ቁጥጥር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣ ነው፤ ያሉትን የሟቾች ቁጥር አልተቀበሉትም፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በዋይት ሐውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በጉዳት ቁጥሮች ላይ ምንም ዓይነት እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በግጭት ውስጥ ሊደርሱ ስለሚችሉ ጉዳቶች አይቀሬነት ፕሬዚዳንቱ ገልጸው፣ ይልቁንም እስራኤላውያንና ፍልስጥኤማውያን በሰላም አብረው እንዲኖሩ፣ ራሱን ለቻለ የእስራኤል እና የፍልስጥኤም መንግሥት መመሥረት አስፈላጊነት አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

ባይደን፣ በሐማስ ቁጥጥር ሥር ስላሉት ከ200 በላይ ታጋቾችም፣ ስጋት እንደገባቸው አመልክተዋል።

ታጋቾችን ለማስለቀቅ ስላለው ድርድር አስቸጋሪነት የገለጹት ባይደን፣ በግብጽ እና በኳታር በኩል ከታጣቂው ቡድን ጋራ ቀጥተኛ ያልኾነ ውይይት እየተካሔደ ነው፤ ብለዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG