የየመን አማፂያን ወደ ቴል አቪቭ፣ እስራኤል ዛሬ ረቡዕ ሚሳዬል ማስወንጨፋቸውን አስታውቀዋል። ጥቃቱ የአደጋ ማስጠንቀቂያ እንዲደወል ሲያደርግ፣ ጉዳት ግን አላደረሰም ተብሏል።
የእስራኤል ሠራዊት በበኩሉ ሚሳዬሉ ድንበር ከማቋረጡ በፊት መመታቱን አስታውቋል።
ሁቲዎች ሚሳዬል ሲያስወነጭፉ በሁለት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በጋዝ ሰርጥ እስራኤል በምታካሂደው ጦርነት ከፍልስጤማውያን ጋራ ያላቸውን አንድነት ለማሳየት እንደሆነ የሁቲ አማጺያን አስታውቀዋል።
በእስራኤል ላይ ሚሳዬል ከማስወንጨፍ በተጨማሪ፣ ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት በመፈጸማቸው ቁልፍ የሆነው የንግድ መርከቦች መተላለፊያ ተስተጓጉሏል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት በበኩላቸው በኢራን በሚደገፉት ሁቲዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ በመዛት ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል የእስራኤል ሠራዊት ባደረገው ምርመራ፣ ሠራዊቱ በጋዛ በመገኘቱ ምክንያት ባለፈው ነሐሴ ስድስት ታጋቾች መሞታቸውን ትላንት አስታውቋል። እንደ ምርመራው ውጤት ከሆነ፣ ሠራዊቱ መግባቱን ተከትሎ፣ ሐማስ አንድ ትውልደ እስራኤል የሆነ አሜሪካዊን ጨምሮ ስድስት ታጋቾችን ለ330 ቀናት ከያዙ በኋላ ገድለዋል።
እስራኤል በጋዛ በምታካሂደው ጦርነት እስከ አሁን 45 ሺሕ ሰዎች እንደተገደሉ የፍልስጤማውያኑ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያስታውቃል።
መድረክ / ፎረም