በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢራንና ስድስቱ ኃያላን ቁልፍ ማዕቀፍ ላይ ተስማሙ


የኑክሌር ስምምነት ላይ በሚያደርሱ ቁልፍ መስፈርቶች ላይ ስምምነት መደረሱን ሐሙስ ምሽት ላይ ይፋ ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ባለሥልጣናት በሎዛን ስዊትዘርላንድ ላለፉት ስምንት ቀናት ሲደራደሩ ከሰነበቱ በኋላ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞኼሪ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞኼሪና የኢን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ የስምምነቱን መደረስ በጋራ ባስታወቁበት ወቅት።
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞኼሪ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞኼሪና የኢን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃቫድ ዛሪፍ የስምምነቱን መደረስ በጋራ ባስታወቁበት ወቅት።

የኑክሌር ስምምነት ላይ በሚያደርሱ ቁልፍ መስፈርቶች ላይ ስምምነት መደረሱን ሐሙስ ምሽት ላይ ይፋ ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ባለሥልጣናት በሎዛን ስዊትዘርላንድ ላለፉት ስምንት ቀናት ሲደራደሩ ከሰነበቱ በኋላ ነው።

ሁለቱ ወገኖች ዛሬ የተፈራረሙት የመጨረሻ የስምምነት ሰነዱን ሳይሆን የፊታችን ሰኔ 23/2007 ዓ.ም እንዲፈረም የሚዘጋጀው የስምምነት ሠነድ ወሣኝ መሥፈርቶች ላይ ነው።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በማዕቀፉ ነጥቦች ላይ ስምምነት መደረሱ እንደተገለፀ ከዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት በሰጡት መግለጫ “ይሄ የስምምነት ሠነድ ኢራን የኒኩሌር መርኃ ግብሯ ሠላማዊ መሆኑን እንድታረጋግጥ ዕድል ይሰጣታል” ብለዋል።

ሚስተር ኦባማ አክለውም “ኢራን ዓለም አቀፍ ኃላፊነቶቿን ከተወጣች የማኅበረሰቡ አካል መሆን እንድምትችል ያሳያል። ይሄ ለኢራንም ለዓለም አቀፍ ሰላምም መልካም ዜና ይሆናል” ብለዋል፡፡

“አሁንም ከዚህ በፊት የቆዩ ሥጋቶችና ልዩነቶች ይቀጥላሉ” ያሉት ፕሬዚደንት ኦባማ ኢራን የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገሮችን “በእጅ አዙር ታጣቂዎች ማመሷ፣ የሽብር ድርጅቶችን መርዳቷ፣ የዩናይትድ ስቴትስ አጋሮችና ሸሪኮችን፤ በተለይ ደግሞ እሥራዔልን ማስፈራራቷ ዛሬም ያሠጋናል፡፡ በዚህ ረገድም እንዲህ ያሉ ተግባሮችን ከጥንስሱ ለመቀልበስና የወዳጅ አጋሮቻችንን ጥቅም ለማስጠበቅ ጠብቀን እንቆማለን።” ብለዋል የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት፡፡

ሲደራደሩ የቆዩትና የቅድሚያ ስምምነቱን ሠነድ የተፈራረሙት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪና የኢራኑ አቻቸው ጃቫድ ዛሪፍ ናቸው።

ስምምነቱ የኢራንን የኒኩሌር ኃይልን የማበልፀግ አቅም በእጅጉ እንደሚቀንስ ገልፀው ሃገሪቱ የሚኖራት ብቸኛው የኃይል ማበልፀጊያ ናታንዝ በሚባለው ሥፍራ የሚገኘው ብቻ እንደሚሆን የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ፌዴሪካ ሞኼሪ አስታውቀዋል፡፡

ኢራን የሚጠበቅባትን መፈፀሟ እንደተረጋገጠ ዩናይትድ ስቴትስና የአውሮፓ ኅብረት ቴህራን ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች ሁሉ እንዲያነሱም ስምምነቱ ያዝዛል፡፡

የኢራን ፕሬዚዳንት ሃሰን ሮውሃኒ እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃን ኬሪ በተናጠል ባወጧቸው የትዊተር መልዕክቶች በውሉ አበይት አምዶች ላይ ስምምነት ላይ መደረሱን አረጋግጠዋል፡፡

ከኢራን ጋር ለድርድር የተቀመጡት አምስቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላት ዩናይትድ ስቴትስ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ሩሲያና ቻይና የምክር ቤቱ ቋሚ አባል ያልሆነችውን ጀርመንን ጨምረው ነው፡፡

ኢራን የኒኩሌር መርኃግብሯን የምታካሂደው “…ሙሉ በሙሉ ለሰላማዊና ለሲቪል ልማት ጉዳይ ብቻ ነው…” እያለች ስትጎተጉት ኖራለች፡፡

/የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በማዕቀፉ ላይ የስምምነቱ መደረስ እንደተነገረ ከዋይት ሃውስ ቤተመንግሥት ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ቃል (በእንግሊዝኛ) ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡/

XS
SM
MD
LG